
የዘመን መቁጠሪያ ገጾች ሲገለጡ እና የታሪክ ማኅደር ሲፈተሽ እንደ ነሐሴ 12 የኢትዮጵያን ማህፀን በክብር የባረከች፣ የነፃነትን ጽንስ በአንድ ዕለት አቅፋ ያበረከተች ሌላ ቀን ማግኘት ይከብዳል። ይህች ዕለት ተራ የፀሐይ መውጫ እና መጥለቂያ ብቻ አይደለችም፤ ይልቁንም የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ቀንዲል የኾነችው ሀገር የህልውናዋን መሰረት የምታጸናበትን ሦሥት የክብር ዐምዶች የተረከበችባት የተቀደሰች የልደት ዐውድማ እንጂ።
የክረምቱ ዝናብ ምድሪቱን በሚያረካባት በዚህች ዕለት የሀገር አባት፣ የጥበብ እናት እና የጦር ግንባር ነበልባል በአንድ የዕጣ ፈንታ ክር ተገምደው ወደ ምድር መጡ።
በነሐሴ 12/1836 ዓ.ም ዕለት በመጀመሪያ ብቅ ያሉት የተበታተነውን የሀገር ገላ በጥበብ ክር የሰፉት፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ዐምድ አጼ ምኒልክ ናቸው። ውልደታቸውም በሰሜን ሸዋ ዞን በአንጎለላ ወረዳ ነው። አጼው በረቂቅ የፖለቲካ ጨዋታ የአውሮፓን ተኩላዎች ያንበረከኩ፣ በዝምታቸው ውስጥ ነጎድጓድን ያረገዙ ታላቅ መሪ ነበሩ።
የሀገርን ዳር ድንበር በልባቸው ጽላት ላይ የቀረፁ፣ የቴክኖሎጂን ብርሃን (ስልክን፣ ባቡርን፣ ዘመናዊ ትምህርትን….) ወደ ኋላ ቀርቷል ተብሎ ይታሰብ ወደ ነበረው የዓለም ክፍል ያመጡ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትቆም ያደረጉ የታሪክ ማገር ናቸው። ምኒልክ ሲወለዱ ኢትዮጵያ የነፃነቷን ጋሻ አብራ ተላበሰች፤ የትዕግስት እና የሩቅ አሳቢነት ፀጋንም ተቀዳጀች።
ነሐሴ 12 የነፃነትን ጋሻ ብቻ አልሰጠችንም፤ የጋሻውን ጥንካሬ የሚፈትኑ ጠላቶችን በብልሃት የምትመክት የጥበብ ፀሐይም አበርክታልናለች። የእቴጌዋ ውልደት 1832 ዓ.ም በጌምድር ደብረ ታቦር ከተማ ነው።
እቴጌ ጣይቱ የውጭ ወራሪዎችን የተንኮል ድር እንደ ሸረሪት ክር የበጠሱ የኢትዮጵያ ሴቶች የክብር ዘውድ ናቸው። “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ሀገሬን ከሚነካ…” ብለው የተንኮሉን የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 በቆራጥነት የረገጡ የሀገር እናት ናቸው።
በመቀሌ ከበባ የጠላትን ጉሮሮ በውኃ ጥም የቆለፉ፣ በዓድዋ የጦር ግንባር የነፃነት ፀሐይ ኾነው ያበሩ፣ የሴትነትን ልስላሴ ከብረት ጥንካሬ ጋር አዋህደው የያዙ የአልበገርባይነት ህያው ተምሳሌት ናቸው። ጣይቱ ማለት የውበት እና የብልሃት፣ የፍቅር እና የቁጣ ፍፁም ውህደት ነበሩ።
የነሐሴ 12ን የሦሥትዮሽ ሚስጥር ፍፁም የሚያደርገው የነዚህን ሁለት የጥበብ እና የፖለቲካ ምሰሶዎች ራዕይ በክንድ ኅይል እና በደረት ግንብነት ያጀበው የጦር አበጋዝ መፈጠሩ ነው። በፈረስ ስማቸው “አባ ጎራው” የተወለዱት ነሐሴ 12/1836 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን በተጉለት እና ቡልጋ በአንጎለላ አስታይ ቀበሌ ነው።
በጠላት ጦር ላይ ጥይትን እንደ ጤዛ እየተራመዱ ምሽግ ያፈራረሱ፣ “እኔን ያየህ ወደፊት!” ብለው የጠላትን ሠራዊት እንደ ቅጠል ያረገፉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ነበልባል ናቸው።
የሀገር ክብር በወረቀት ላይ በሚፃፍ ስምምነት ብቻ ሳይኾን አጥንትን በመከስከስ እና ደምን በማፍሰስ የሚረጋገጥ መኾኑን በአምባላጌ እና በዓድዋ ተራሮች ላይ በደማቸው የፃፉ የጀግንነት መለኪያ ናቸው። እሳቸው ወደ ጦር ሜዳ ሲገቡ ሞትን የናቁ፣ ሀገርን ግን ከህይወታቸው በላይ ያፈቀሩ ታላቅ መስዋዕት ነበሩ።
ነሐሴ 12 የዓድዋን ደማቅ ድል እውን ለማድረግ የዘመን ቀማሪው እጁን ዘርግቶ የጥበብን፣ የጀግንነትን እና የአመራርን ክሮች በአንድ ማዕቀፍ የሸመነባት ዕለት ናት።
ቀኗ በኢትዮጵያ የዘመን ሰሌዳ ላይ ዝም ብላ አታልፍም፤ ይልቁንም ሉዓላዊነታችንን አቅፋ የሳመችበት የነፃነት ዜማ ከትውልድ ትውልድ ሲዘመር የሚኖር ህያው የክብር ሀውልት ኾና የምትዘከር እንጂ።
ምንጭ፦ ኢትዮጵያን ፓትሪዎት ዶት ኦርግ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
