የአማራ ክልል የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ የመሠብሠብ እና ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራው 80 በመቶ ደርሷል።

6
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የመንግሥት ሠራተኞች መረጃ ማረጋገጥ እና የዲጂታላይዜሽን ሥራ ወደ ትግበራ መግባቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ካሳ አበባው በአማራ ክልል የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ የመሰብሰብ፣ የማጥራት እና ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ አሁን ላይ 80 በመቶ አፈጻጸም ላይ እንደደረሰ ገልጸዋል።
በሀገር ደረጃ የተጀመረው ይህ የመረጃ ማሠባሠብ እና ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ፖሊሲ ሪፎርም ዋና አካል መኾኑንም ተናግረዋል። ለወደፊቱ ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ግንባታም መሠረት የሚጥል እንደኾነ ጠቅሰዋል።
የመረጃ ማሠባሠቡ እና የማጥራቱ ሥራ ሁለገብ መረጃን ያካተተ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊዋ የሠራተኛ ስም፣ የሥራ መደብ፣ የሥራ ደረጃ፣ የደመወዝ መጠን እና የሚሠራበት ተቋም በአካል ተገኝቶ ማረጋገጫ (ፊርማ) በመስጠት መረጃው የሚሠበሠብበት አሠራር እንዳለውም አንስተዋል።
እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ተቋማት እና የሰው ኃይል ያለባቸው እና የሌለባቸው የሥራ መደቦች አስቀድመው ወደ ተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ አሥተዳደር መረጃ አያያዝ ሥርዓት (ISMIS) ሲስተም እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል።
ከአፈጻጸም እና ቀጣናዊ ልዩነት አኳያ የመረጃ መሠብሠቡ ሥራ 80 በመቶ መደራጀቱን እና የማረጋገጥ ሥራው ደግሞ 78 በመቶ መድረሱንም ጠቅሰዋል።
የደብረ ብርሃን እና የደሴ ቀጣናዎች የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግበዋል ነው ያሉት። በጎንደር እና ባሕርዳር ቀጣናዎች ደግሞ ሥራውን ለማፋጠን ልዩ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። በሂደቱ የሲስተም ተደራሽነት፣ የኔትወርክ እና የመብራት መቆራረጥ፣ የሠራተኞች የእንቅስቃሴ ችግር እና የመምህራን የክረምት እረፍት በወቅቱ ለማጠናቀቅ ችግሮች እንደነበሩም አንስተዋል። ችግሮቹን ቴክኖሎጅ (በቨርቿል) ግምገማ እና ከፌዴራል ተቋማት ጋር በመቀናጀት የመፍታት ሥራ ተሠራቷል ብለዋል።
ዲጂታላይዜሽኑ በዋናነት ለሠራተኞች የወደፊት ሀገራዊ የደመወዝ ጭማሪ እና ጥቅማጥቅሞችን በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሠርቶ ለመወሰን እና በማንኛውም ሰው ሊታይ የሚችል መታወቂያ (Public ID) ለማግኘት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ለአገልግሎት አሰጣጡም የሠራተኞችን ፍላጎት እና የችሎታ ክፍተት በጥናት በመለየት ትክክለኛ የትምህርት እና የቴክኒክ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ቀልጣፋ እና ከሰው ንክኪ ነጻ የኾነ ዲጂታል አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ መሠረት እንደሚኾንም ተናግረዋል።
የማረጋገጥ ሥራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ በየደረጃው ያሉ መሪዎች፣ የሲቪል ሰርቪስ ባለሙያዎች እና የስታቲስቲክስ አገልግሎት ሠራተኞች በትጋት እየሠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል። በተቀመጠው ቀን የማይጨርሱ ሠራተኞች ላይ የሚሰጠው ውሳኔ በሀገር ደረጃ ከፌዴራል የሚወሰን እንደሚኾንም ጠቁመወል።
✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየነጻነት ጠባቂዎች፣ የጸናች ሀገር አውራሾች
Next articleነሐሴ 12 – የነፃነትን የሦሥትዮሽ ዐምድ የወለደችው የክብር አጥቢያ