የነጻነት ጠባቂዎች፣ የጸናች ሀገር አውራሾች

6
በቤት ውስጥ ባል እና ሚስት፣ በዙፋን ላይ ንጉሥ እና ንግሥት ናቸው። ሀገርን በጥበብ መርተዋል፤ ነጻነትን ጠብቀዋል፤ ሉዓላዊነትን አስከብረዋል፤ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጥቁሮች ተስፋ ኾነዋል። ትውልድን በሀገር ፍቅር ቀርጸዋል፤ ለአንድነት አነሳስተዋል፤ ኢትዮጵያዊነትን፣ አይደፈሬነትን፣ ጀግንነትን፣ ብልሃትን እና ጥበብን በረቀቀ ቀለም በታሪክ ብራና ላይ ጽፈዋል።
የቅኝ ገዢዎችን ያልተገራ ፍላጎት ገትተዋል፤ ቅኝ ገዢን በጠነከረ ክንዳቸው ሰብረዋል፤ ኢትዮጵያን በዓለሙ ፊት ጠላቶቿ እንዲፈሯት፤ ወዳጆቿ እንዲያከብሯት፤ መመኪያ እና መጠጊያ እንድትኾን አድርገዋል።
በጥበብ እየመከሩ፣ በብልሃት እየዘከሩ ኢትዮጵያን አስጊጠዋል፤ የከበረውን ታሪክ ሠርተዋል፤ ትውልድ ሁሉ የሚያወድሰውን ገድል ፈጽመዋል፤ በዓለም ታሪክ የቅኝ ግዛትን አስተሳሰብ የቀበረውን የረቀቀ አሻራ አኑረዋል።
ኢትዮጵያ በእነርሱ ተደስታለች፤ አፍሪካም በእነርሱ ኮርታለች። ስለ ምን ቢሉ ነጻነትን በጀግንነት ጠብቀዋል፤ የከበረች ሀገርን ከእነ ክብሯ ለትውልድ አስተላልፈዋል፣ ጥቁሮች ሁሉ ለነጻነት እንዲነሳሱ መንገድ ጠርገዋል፤ ብርሃን አብርተዋልና። የዘመናት ጀግኖች፣ የዘመናት አብሪ ኮኮቦች እምዬ ምኒልክ እና ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ።
ንጉሡ እና ንግሥቷ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የጎላ ስም አላቸው። ዓድዋን የመለሰ ድል የሰጡ፣ ኢትዮጵያን ለማዘመን የተጉ፣ በዓለም ፊት የተፈራች እና የተከበረች ያደረጉ ብልሆች እና ጀግኖች ናቸው።
አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ሲጋቡ ቤተ መንግሥቱ ውቃቢ ገባው፣ ግርማ እና ውበት ተጫነው፤ ጥላው ከበደ፣ የእውነተኛ አዱኛ፣ የእውነተኛ ደስታ ገባ ይላሉ። አባ ዳኘው ምኒልክ ጣይቱ ብጡልን ካገቡ በኋላ ያባ ዳኘው መንግሥት ወዲያው እያደረ ሰፋ፣ ተሳፋ፣ ገነነ፣ ተሞገሠ፣ ከግርማ ላይ ግርማ ጨመረ ብለዋል።
ጣይቱ የመከሩት ሀገር የሚያሳድር፣ የተናገሩት ከምድር ጠብ የማይል፣ ለባለቤታቸው መልካም ደጋፊ፣ ለኢትዮጵያ ጋሻ ናቸው ይላሉ።
እነዚህ ንጉሥ እና ንግሥት የሀገሬው ሰው “ባል እና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቅዳሉ” የሚለውን ብሂል ያሳመሩ ብቻ አይደሉም በአንድ ቀን የተወለዱ ድንቅ ታሪክ ያላቸው ናቸው እንጂ።
ተክለጻድቅ መኩሪያ አጼ ምኒልክ እና ኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው ምኒልክ በነሐሴ 12/1836 ዓ.ም አንጎለላ ኪዳነ ምሕረት መወለዳቸውን ጽፈዋል። ከአባታቸው ከንጉሥ ኃይለ መለኮት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ እጅጋየሁ ጋር በአንጎለላ፣ በአንኮበር እና በደብረ ብርሃን እየተዘዋወሩ አድገዋል ይላሉ።
ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል አጭር የሕይወት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው እቴጌ ጣይቱ በነሐሴ 12/1832 ዓ.ም በጌምድር ውስጥ ደብረ ታቦር ከተማ ተወለዱ። ተጠምቀው ክርስትና የተነሡት በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ነው። በልጅነት ዘመናቸው በዚሁ ደብር ውስጥ ዳዊትን ተምረዋል ብለው ጽፈዋል።
እኒህ ንጉሥ እና ንግሥት በመመካከር ሀገር ያጸኑ፣ በብልሃት ሀገር ያኮሩ ናቸው። እምዬ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ በብልሃት እና በጀግንነት ኢትዮጵያን መርተው፣ ቅኝ ገዢዎችን ድል መትተው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አዳዲስ ሥልጣኔዎችን መሠረት ጥለው ያለፉ ጀግኖች ናቸው።
የኢትዮጵያን አንድነት በጽኑ አለት ላይ ያጸኑ፣ ነጻነትን እንዳይጠፋ አድርገው ያበሩ፣ ለትውልድ መመኪያ የኾነ የድል ውርስ የሰጡ፣ ሉዓላዊነትን ያስከበሩ፣ ከሀገራቸው አልፈው ለአፍሪካውያን የነጻነት አባት እና እናት የኾኑ ንጉሥ እና ነገሥት ናቸው።
ከሠሯቸው ሥራዎች፣ ከፈጸሟቸው ገድሎች፣ ለትውልድ ካወረሷቸው የታሪክ ውርሶች ሁሉ ዓድዋ የላቀው ነው። ስለ ምን ቢሉ ዓድዋ የዓለምን የፖለቲካ እና የታሪክ አረዳድ የቀየረ ሕያው ድል ነውና።
አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ከዓድዋ ጦርነት ወዲህ የኢትዮጵያ ስም ፀሐይ ባየው ሀገር ሁሉ ታወቀ፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ምንም ከጥንት ከመሠረት ጀምራ ራሷን ችላ ብትኖር ከቶውንም ከባሕር ወዲያ እስከ ምስር በአንድ ወገንም እስከ አደን ከአረብ ሀገር ተሻግራ ብትገዛ፣ በአውሮፓ ስሟ የአሕዛብ ሀገር ናት ትባል ነበረ፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ኃይል፣ በዳግማዊ ምኒልክ ዕውቀት ዛሬ ግን ኢትዮጵያ የእውነተኛ ስሟ ተገለጠ። ከእውነተኛ መዓረጓ ገባች፡፡ የኢትዮጵያ ዓለም ከዓድዋ ጦርነት ወዲህ ተጀመረ፡፡ እቴጌ ጣይቱ እና ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያን በጋራ አሳመሯት፣ ክብሯንም ገለጡላት ብለው ጽፈዋል።
ቀኝ አዝማች ታደሰ ዘወልዴ አጼ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ተደጋግፈው በጦሩም ኾነ በሰላሙ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ታሪክ መሥራታቸውን ጽፈዋል። እቴጌ ለምኒልክ ሚስታቸው ብቻ አልነበሩም እህታቸው፣ አማካሪያቸው ነበሩ እንጂ። በቤት ውስጥ የሚስትነት ሚናቸውን፣ በዙፋን ላይ የንግሥትነት ሚናቸውን በአግባቡ የተወጡ ነበሩ።
እምዬ ምኒልክም የእቴጌን ምክር የሚሰሙ፣ በባለቤታቸው ብልህነት የሚተማመኑ ነበሩ። የጣይቱ ብርታት፣ የእምዬ ምኒልክ አስተዋይነት፣ የሕዝቡ ሀገር ወዳድነት እና ቆራጥነት ኢትዮጵያን ከጠላት ተከላከላት፣ ነጻነቷን አስጠበቃት፣ አንድነቷንም አደረጀላት።
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 ዓ.ም በተሰኘው መጽሐፋቸው በቅርብ ዘመን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዝናን የሰጠ ድርጊት ማሰብ ያዳግታል። የቅኝ አገዛዝን ማዕበል የገታ አንድ ትልቅ ድርጊት እንደመኾኑ ሁሉ የቅኝ ገዥዎችን ቅስም የሰበረውን ያህል የተገዥዎችን አንገት ደግሞ ከተደፋበት ቀና እንዲል ያደረገ ክስተት ነበር ሲሉ አትተዋል፡፡
በዚህ ድል ምክንያትም የፖለቲካ መሪዎችም ኾኑ ነጋዴዎች አቋማቸውን እንደገና እንዲመረምሩ ተገደዱ ብለው ጽፈዋል። ይህን ድል ያመጡት በአንድ ቀን የተወለዱት እምዬ እና እቴጌ ናቸው።
ጥቁሮች በዓለም ፊት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ያደረጉት እነዚህ ንጉሥ እና ንግሥት ልደታቸው ዛሬ ናት። ነሐሴ 12 ቀን።
የነጻነት ጠባቂዎች፣ የጸናች ሀገር አውራሾች ንጉሥ እና ንግሥት ኾይ እንኳን ተወለዱ። ኢትዮጵያ በእናንተ መወለድ ተደስታለች። በእናንተ ንግሥና ተከብራለች፤ በታሪካችሁም ስትኮራ እና ስትመካ ትኖራለች።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየመንግሥት እና የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር በተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል።
Next articleየአማራ ክልል የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ የመሠብሠብ እና ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራው 80 በመቶ ደርሷል።