የመንግሥት እና የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር በተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል።

8
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን ከባለድርሻ አካላት ጋር የገመገመ ነው። በበጀት ዓመቱ የመንግሥት እና የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር በተከናወኑ የሕግ፣ ፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስታውቋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በግምገማ መድረኩ ላይ እንደገለጹት በሕግ እና ፍታብሔር ዘርፍ ክልላዊ የፍትሐ ብሔር ስትራቴጂ በማዘጋጀት የአሠራር ሥርዓቶችን ማሻሻል ተችሏል። በዚህም በፍርድ ቤት ተከራክሮ የማሸነፍ ምጣኔን በማሳደግ፣ ውሳኔ ከተሰጠበት 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ውስጥ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብሩን ተከራክሮ ማሸነፍ ተችሏል ነው ያሉት።
በፍርድ ማስፈጸም ሂደት ከተወሰነው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ውስጥ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብሩ ለመንግሥት ገቢ ኾኗል ብለዋል።
በሰነዶች፣ በጠበቆች እና በሲቪክ ማኅበራት አገልግሎት ዘርፍ ከ669 ሺህ 600 በላይ ተገልጋዮችን በማስተናገድ እና ከ394 ሺህ 600 በላይ ሰነዶችን በማረጋገጥ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠቡ ተገልጿል።
የሕግ አወጣጥን ፍትሐዊ እና ተገማች ለማድረግ በተደረገው ጥረትም በበጀት ዓመቱ 15 አዋጆች፣ 65 ደንቦች እና 31 መመሪያዎች በጠቅላላው 111 ሕጎች በጥራት እና በፍጥነት መዘጋጀታቸውን አንስተዋል። 142 መመሪያዎች ደግሞ ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
በወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር በኩል ወንጀልን ለመከላከል እና የተመዘበረ ንብረትን ለማስመለስ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን የጠቀሱት ኀላፊው ከፖሊስ የቀረቡ ከ22 ሺህ 800 በላይ የምርመራ መዛግብት ውስጥ ከ21 ሺህ 700 በላይ መዛግብት ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል ብለዋል። ውሳኔ ካገኙ 9 ሺህ 609 መዛግብት መካከልም ቢሮው በ8 ሺህ 727ቱ በማሸነፍ የላቀ ውጤት አስመዝግቧል።
በ2019 በጀት ዓመትም የሕግ የበላይነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የአሠራር እና የሥነ-ምግባር ብልሽቶችን ለማረም ፣ ውዝፍ መዛግብትን በማጣራት የመንግሥት እና የሕዝብ ጥቅም እንዲከበር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቋል።
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከጥርስ መፋቂያ ሽያጭ እስከ ሃብት ማማ – የሥራ ፈጣሪነት ተምሳሌት
Next articleየነጻነት ጠባቂዎች፣ የጸናች ሀገር አውራሾች