ከጥርስ መፋቂያ ሽያጭ እስከ ሃብት ማማ – የሥራ ፈጣሪነት ተምሳሌት

18
“የችግር ጽናት ለፍሬ ያበቃል” እንደሚባለው የዛሬዋ ባለታሪካችን በገጠሟት ውጣ ውረዶች አልተበገረችም፤ ይልቁንም የበለጠ እየበረታች አሁን ላይ የላቀ የገቢ ምንጭ ማማ ላይ ትገኛለች – አጸደ አጥናፉ።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በባሕል አልባሳት ዘርፍ ተሠማርታ ትገኛለች፤ በዘርፉም ከሽመና እስከ ጥልፍ በማቀናጀት ጥራት ያላቸው የባሕል አልባሳትን ለገበያ እያቀረበች መኾኑን አጫውታናለች።
የሥራ ጉዞዋን የጀመረችው በልጅነቷ ሲኾን የወላጅ አባቷ በሞት መለየት ለእርሷ እና ለቤተሰቧ ከባድ ፈተና ገጥሟት ነበር። እናቷን ለመደገፍ እና ቤተሰቧን ለማሥተዳደር በሰባት ዓመት ዕድሜዋ ሎሚ እና የጥርስ መፋቂያ በመሸጥ የዕለት ከዕለት ኑሮ ትታገል ጀመር።
ኑሮ ሲከብዳትም ትምህርቷን ለመቀጠል ወደ ዘመዶቿ ዘንድ ወደ ሌላ ቦታ አምርታለች። ከዚያም ዩኒቨርሲቲ በመግባት ከትምህርቷ ጎን ለጎን የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ችላለች።
ሥራ ፈጣሪዋ እንደተናገረችው ሴት ልጅ እውነተኛ ሰላም የምታገኘው በእጇ ሠርታ ገንዘብ ማግኘት ስትችል ነው የሚለውን የጽናት መርሕ አጥብቃ ይዛ ቀጥላለች። ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀች በኋላም በአዲስ አበባ በጋርመንት ሥራ ላይ ተሠማርታ እንደነበር አውስታለች። ይሁን እንጂ የሥራ ሁኔታው ባለ መመቻቸቱ ምክንያት ወደ ባሕር ዳር አቀናች።
​ከዚያም በባሕር ዳር ጥናት በማድረግ የባሕል አልባሳት ሥራን ለመሥራት መረጠች። ስለ ዘርፉ በቂ ሥልጠና ከወሰደች በኋላ አነስተኛ ሱቅ በመከራየት መሥፋት እና መጥለፍ ጀመረች። መጀመሪያ ላይ ገዥ ማግኘት ፈታኝ ኾኖባት ነበር፤ ይሁን እንጂ ሥራውን ወደ ኦንላይን በማስገባት ጠንካራ የደንበኛ መረብ መገንባት ችላለች።
​አሁን ላይ ሥራዋን በማስፋት “አጼ ጥበብ” በሚል ስያሜ ከፍታ እየሠራች ነው። በፊት ከሌሎች በመግዛት ትሸጥ የነበረ ቢኾንም አሁን ላይ ከሽመና ጀምሮ እስከ ጥልፍ እና ዝግጁ ሽያጭ ድረስ በራሷ አዘጋጅታ ለደንበኞች እያቀረበች መኾኑን አጫውታናለች። ከባሕር ዳር ባለፈም በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በመክፈት ሥራውን አስፍታለች።
በ35 ሺህ ብር ብቻ የተጀመረው ይህ የባሕል አልባሳት ንግድ ሥራ ዛሬ ከ20 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥራለች። በልጅነቷ በሰባት ዓመቷ የጀመረው የዕድገት ትግል እና ሥራ ወዳድነት ዛሬ ላይ ለታላቅ ስኬት እና ዝና አብቅቶኛል ትላለች።
በሥራ ሂደቷ እጅግ ብዙ ውጣ ውረዶችን በጽናት ያላለፈችው ሥራ ፈጣሪዋ አጸደ፣ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ለንግዷ ዕድገት ትልቅ ድርሻ አበርክቶልኛል ነው የምትለው። የማኅበረሰቡ የባሕል አልባሳት የመጠቀም ልምዱ እያደገ መምጣቱንም ትናገራለች። ለወደፊትም የተሰማራችበትን ሙያ በዘመናዊ መልኩ ለማስፋፋት፣ በፋብሪካ ደረጃ ለማምረት እና ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዳ እየተጋች ነው።
በአጸደ የባሕል አልባሳት ተቀጥሮ በጥልፍ ሙያ እየሠራ የሚገኘው ብሩክ ከበደ በፊት ይስተዋሉበት የነበሩ ችግሮችን እንደፈታለት ነግሮናል። በሥራውም ደስተኛ መኾኑን ገልጿል።
ከአራት ዓመት በላይ አብሮ እየሠራ መኾኑን የሚናገረው ወጣት ብሩክ አጸደ ጠንካራ፣ ታታሪ እና ለሌሎች አርዓያ መኾኗን ይገልጻል። ከትንሽ ነገር ተነስቶ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል የምታሳይ ምሳሌ መኮኗን መስክሮልናል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከቀጣናዊ ስጋቶች በላይ ከፍ ብሎ የተቀመጠው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት
Next articleየመንግሥት እና የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር በተከናወኑ ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል።