ከቀጣናዊ ስጋቶች በላይ ከፍ ብሎ የተቀመጠው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት

14
🇪🇹
ብሔራዊ ጥቅም የአንድ ሀገር ሕልውና ዋና ቋጠሮ ነው። የሉዓላዊነት መከበር፣ የሁለንተናዊ ደኅንነት ዋስትና፣ የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ሞተር፣ የዲፕሎማሲ ማሳለጫ ዋና መሣሪያም ነው።
ይህ ብሔራዊ ጥቅም የሚረጋገጠው እና የሚከበረው በተቀናጀ የሕዝብ ተሳትፎ፣ በቁርጠኛ መንግሥታዊ መዋቅር ብሎም በስጋቶች ልክ በሠለጠነ የሰው ኀይል በሚመራ፣ በቴክኖሎጅ በታገዘ እና ዘመኑ የሚጠይቀውን የጦር መሣሪያ በታጠቀ ዝግጁ ወታደራዊ ተቋም ሲጠበቅ ብቻ ይኾናል።
የአፍሪካ የኢኮኖሚ መሪ እና የሰላም ዘብ የመኾን ትልም የያዘችው ኢትዮጵያም ትልሟን ለማስመር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለይታለች። የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥም የብሔራዊ ጥቅሞቿ ኹሉ ቁንጮ ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል።
ይህ ተራ ፖለቲካዊ ጉዳይ ሳይኾን የኢትዮጵያን ሰላም እና ዕድገት ከማረጋገጥ እስከ ቀጣናዊ የሰላም ዋስት መኾን ድረስ የተዘረጋ ርዕይ የተሰነቀበት ዋና አጀንዳ ነው።
ኢትዮጵያ ይህን የትውልድ አጀንዳ መልስ ለመስጠት የሀገር መከላከያ ሠራዊቷን አሁን ካለው የጂኦ ፖለቲካዊ ተለዋዋጭነት እና ከቀጣናው ሁኔታ አኳያ ራሱን በሠለጠነ የሰው ኀይል፣ በቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ የጦር መሣሪያ አጎልብቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ሕልውና እና ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብርበት አስተማማኝ መሠረት ገንብቷል።
💂የሠራዊቱ ከቁጥር ብልጫ የተሻገረ የሰው ኀይል ግንባታ ተቋሙ ቁጥራዊ ብልጫን ብቻ ሳይኾን የአዕምሮ እና የአካል ብቃትን ያጣመረ ኀይል ለመቅረጽ በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል። የሰው ኀይል ግንባታው ከባሕላዊ የጦርነት ስልት የወጣ በወታደራዊ ሳይንስ እና በስትራቴጂክ ዕውቀት በተሞሉ መሪዎች መኮንኖች እና ተዋጊዎች ላይ አተኩሯል።
የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ እና የተለያዩ ወታደራዊ አካዳሚዎች የአመራር ጥበብን፣ ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕግጋትን እና የተራቀቁ ወታደራዊ ሳይንሶችን በማስተማር ላይ ይገኛል። በዚህ አግባብ ሠራዊቱ በማንኛውም ሁኔታ ሕዝባዊ ተልዕኮውን በላቀ ዲሲፕሊን እና በትንሽ መስዋዕትነት በድል እንዲወጣ የሚያስችለውን አቅም እንዲፈጥር አስችሎታል።
🛸 የተቋሙ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሠራዊቱ የጦር ሜዳ ዋስትና ኾኗል።
በዚህኛው ክፍለ ዘመን የጦርነት ድል የሚወሰነው የጦር ሜዳ መረጃን ቀድሞ መቆጣጠር በመቻል እንደኾነ ይነገራል። ይህን ቀድሞ የተረዳው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሳይበር ደኅንነት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እና በዲጂታል የመገናኛ መረቦች ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር አድርጓል።
የምድር ጦሩ፣ የአየር ኀይሉ እና የባሕር ኀይሉ በሳተላይት እና የሬዲዮ መገናኛ ቴክኖሎጅዎች የሚያደርገው የተቀናጀ የመረጃ ልውውጥ በብዙዎች የተደነቀ ኾኗል። ይህም የጦር ሜዳውን ሁኔታ በቀጥታ ለመከታተል እና ፈጣን ስልታዊ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
🚀 የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ሚዛንን የሚያስጠብቀው የሠራዊቱ የትጥቅ አቅም ተቋሙ ራሱን በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ያስታጠቀበት መንገድ የኢትዮጵያን ቀጣናዊ የኀይል ሚዛን ያስጠበቀ እና ያስከበረ ኾኗል።
ማንኛውንም ስጋት በሩቅ የሚያስቀር አቅምንም ፈጥሯል። የምድሩም ኾነ የአየር ኀይሉ እጅግ በዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች፣ ተወንጫፊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ ከባድ መሣሪያዎች፣ ፀረ አውሮፕላን ሚሳኤሎች፣ ዘመናዊ ታንኮች አቅሙን ከመቸውም ጊዜ በላይ አጠናክሯል።
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዛሬ ላይ የደረሰበት የሰው ኀይል ልሕቀት፣ የቴክኖሎጂ ምጥቀት እና ዘመናዊ የውጊያ ስልት ተቋሙን ከቀጣናዊ ስጋቶች በላይ ከፍ አድርጎ አስቀምጦታል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ ጊዜያት ባደረጓቸውን ንግግሮች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰው ኀይል ብዛት ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል እጅግ ዘመናዊ እና የረቀቁ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቀ ስልታዊ ኀይል መኾኑን አስምረውበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአባቶቻችንን ጀግንነት ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማገናኘት የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በማንኛውም ሰዓት እና ቦታ አስተማማኝ ኀይል መኾኑንም አስረግጠዋል።
ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የቁርጥ ቀን ጋሻ መኾኑን በተግባር ያረጋገጠበት ነው። ሌት ከቀን የሚተጋው ይህ ተቋም የሀገሪቱ የልማት፣ የሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ዋነኛ የጀርባ አጥንት ኾኖም ቀጥሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሻደይ – የክረምቱም የገበያውም ድምቀት
Next articleከጥርስ መፋቂያ ሽያጭ እስከ ሃብት ማማ – የሥራ ፈጣሪነት ተምሳሌት