
የሰሜን ሸዋ ዞን ፍትሕ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በክልሉ ለተመዘገቡት ውጤቶች የፍትሕ አካላት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው ገልጸዋል።
የፍትሕ ተቋማት ዋነኛ ኀላፊነት ሕገ ወጥነትን መከላከል በመኾኑ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እና መርህን መሠረት ያደረገ አሠራር በመከተል የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ተቋማዊ አቅምን የማጎልበት ሥራ ውጤታማ እንደነበር ጠቁመው፣ ባለፈው በጀት ዓመት ከ665 ሺህ በላይ ሰነዶች አገልግሎት ማግኘታቸውን እና ከቀረቡ 9 ሺህ 609 መዛግብት ውስጥ 8 ሺህ 727 የወንጀል መዛግብት ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ እና የደብረ ብርሃን ከተማ ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ ተመስገን ዘገየ ሰላምን ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከአጋር አካላት ጋር የተደረገው ቅንጅታዊ ሥራ በ2019 በጀት ዓመትም የታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ ደመረ ቸሬ እንደተናገሩት በዞኑ ከቀረቡ 2 ሺህ 400 መዝገቦች ውስጥ 98 በመቶ የሚኾኑት ውሳኔ ያገኙ ሲኾን በወንጀል የተመዘበረ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብት ማስመለስ ተችሏል።
በተጨማሪም ለ1 ሺህ 300 ወገኖች ነፃ የሕግ አገልግሎት መሰጠቱንም አብራርተዋል።
#አሚኮ #ፍትሕ_ሰሜንሽዋ_አማራክልል #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ደብረ_ብርሃን #መስከረም_07_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
