
በደሴ ጥላሁን ( ዶ.ር) የተጻፈው “ሜሪቶክራሲ” መጽሐፍ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ምሁራን በተገኙበት በባሕር ዳር ከተማ ተመርቋል።
መጽሐፉ ላይ የዳሰሳ ሀሳብ ያቀረቡ ምሁራን ሜሪቶክራሲ ብዙ ቁም ነገሮችን የያዘ የአካዳሚክ መጽሐፍ መኾኑን ገልጸዋል። የውጭ እና የሀገር ውስጥ ልምዶችን በሚገባ የገለጸ መኾኑንም አንስተዋል። ለሀገር ጠቃሚ ሃሳቦችን የያዘ መጽሐፍ እንደኾነም አመላክተዋል።
ፖለቲከኞች፣ ወጣቶች እና ምሁራን ሊያነቡት የሚገባ መኾኑንም ገልጸዋል። መጽሐፉ የትናንቱን የቃኘ፣ ዛሬን የዋጀ እና ነገ ምን መደረግ እንዳለበት የመፍትሔ ሃሳብ ያመላከተ መኾኑንም አንስተዋል።
ሰዎች በብቃታቸው ብቻ መሪ እንዲኾኑ የሚያበረታታ እንደኾነም ነው የተናገሩት። አዲስ የአካዳሚክ መንገድ የተለመ መጽሐፍ እንደኾነም አንስተዋል። መጽሐፉ በተለይም ለሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት አሥተዳደር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ነው ያመላከቱት።
የሜሪቶክራሲ መጽሐፍ ጸሐፊ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) መጽሐፉ ሀገር እና ሕዝብ የሚገባቸውን ክብር እንዲያገኙ የሚያደርግ ትልቅ ሃሳብን የያዘ መኾኑን ገልጸዋል። ለሀገር እና ለትውልድ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። መጽሐፉ የእኔ መኾኑ አብቅቷል፣ ከዛሬ ጀምሮ የአንባቢያን ነው፣ እናንተ ስታነቡት እና ስትከራከሩበት ሙሉ ሕይወት ያገኛል ነው ያሉት።
ሜሪቶክራሲ ብቃት ያለው አሥተዳደር እና ሥርዓት እንዴት መገንባት ይቻላል? የሚለው ላይ ትኩረት ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። መጽሐፉ በቻይና ሀገር የሦሥተኛ ዲግሪያቸውን እየተማሩ ባለበት ጊዜ መጠንሰሱን አስታውሰዋል። በቻይና ሀገር የፖለቲካ ሜሪቶክራሲ ትልቅ ቦታ እንዳለው የተናገሩት ጸሐፊው ከዚህ ጋር የተያያዙ የተለያዩ መጻሕፍትን በማንበብ የመጽሐፉ ሃሳብ መጠንሰሱን አንስተዋል።
ሜሪቶክራሲ የብቃት አሥተዳደር ነው፤ ማንኛውም ዜጋ ክብር፣ ሃብት እና ሥልጣን የሚያገኝበት ምንጭ ብቃት፣ ጥረት፣ ዕውቀት፣ ክህሎት እና ሥነ ምግባር መኾን አለበት፤ ዘር፣ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት እና ሎሎች ጉዳዮች መለኪያ መኾን የለባቸውም የሚል ጽንሰ ሃሳብ ነው ይላሉ።
የሜሪቶክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ሜሪቶክራሲታዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል። ሜሪቶክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት ደግሞ ትምህርት ቀዳሚው ጉዳይ ነው፤ ማንኛውም ዜጋ እኩል የመማር ዕድል እንዲያገኝ ማድረግ፣ ከትምህርት የሚገኘውን ዕውቀት እና ብቃት መነሻ በማድረግ ማኅበረሰብን ማሥተዳደር እንደሚገባ የሚያነሳ ነው ብለዋል።
ሜሪቶክራሲያዊ ሥርዓትን መሸከም የሚችሉ ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል። ነጻ እና ገለልተኛ የሲሺል ሰርቪስ አገልግሎት መገንባት እንደሚገባም ያመላክታል ነው ያሉት።
መጽሐፉ ሜሪቶክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ያለውን ጥቅም እንዳመላከተም አንስተዋል። ለሀገር ግንባታ እና ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ትልቅ ፋይዳ ያለው ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል። ለትውልድ፣ ለተመራማሪዎች እና ለፖሊሲ አውጭዎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት።
መጽሐፉ ለዚህ እንዲበቃ ላገዟቸው እና ምክረ ሃሳብ ለሰጧቸው ሁሉም ምሥጋና አቅርበዋል።
#አሚኮ #የመጽሐፍ_ምረቃ #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ሜሪቶክራሲ #የብቃት_አስተዳደር #ትምህርት #ሲቪል_ሰርቪስ #ሀገር_ግንባታ #አካዳሚክ #መጽሐፍት
#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
