የቴምር ፌስቲቫል በኢትዮጵያ!

4

 

የቴምር ኢንቨስትመንት እና ገበያ ትስስር አቅምን ለማሳደግ ያለመ ፌስቲቫል በአፋር ክልል ሊዘጋጅ ነው። ከመስከረም 10/2019 ዓ.ም እስከ መስከረም 12/2019 ዓ.ም በሚቆየው ፌስቲቫል የቴምር አልሚዎች እና አጥኝዎች የዕውቀት ሽግግር የሚያካሂዱበት ነው ተብሏል።

ቴምር በአሁኑ ጊዜ በአፋር፣ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል እንዲሁም ድሬዳዋ እና ኦሮሚያ ደቡባዊ ክፍል ይመረታል።

ኢትዮጵያ ቴምርን ከውጭ በየዓመቱ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ስታስገባ እንደነበር የግብርና ሚኒስትር ድኤታ አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሐመድ ተናግረዋል። ኾኖም በአሁኑ ጊዜ በሀገር ውስጥ ማምረት በመቻሉ 650 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ምርት ብቻ ታስገባለች ነው ያሉት።

የፌስቲቫሉ ተባባሪ አዘጋጅ የካሊፋ ኢንተርናሽናል አዋርድ ዋና ጸሐፊ ፕሮፌሰር አብዱለሃብ ዛይድ 2ኛው የኢትዮጵያ ቴምር ፌስቲቫል፣ የቴምርን ሳይንሳዊ ልማት ለማበረታታት አጥኝዎች እና አልሚዎች በመሠባሠብ የአቅም ግንባታ እና የዕውቀት ሽግግር የሚያካሂዱበት እና ኢንቨስትመንት የሚያሳድጉበትን ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

የአፋር ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮን ወክለው ሀሩን አሊ በሰጡት ማብራሪያ የሚዘጋጀው የቴምር ፌስቲቫል በአፋር ሲዘጋጅ ክልሉ በብዛት የሚመረትበት እና ብዙ ተጠቃሚ ያለበት አካባቢ በመኾኑ ነው ብለዋል።

የፌስቲቫሉ መዘጋጀት የግብርና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እጅግ ጠቃሚ መኾኑም ተነስቷል።

በኢትዮጵያ ከ500 አስከ 700 ሺህ ሄክታር መሬት የሚኾን ለቴምር ምቹ የእርሻ ስፍራ ቢገኝም 1 ነጥብ 5 በመቶው ብቻ እንደሚለማ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ 10 ዓመት ያላትን 6 ሺህ ሄክታር የቴምር ልማት ወደ 25ሺህ ሄክታር አሳድጎ በማልማት በሄክታር 158 ኩንታል በማምረት የገቢ ምርትን ለመተካት የሚያስችል ዕቅድ ተይዞ በትግበራ ላይ መኾኑም በመግለጫው ተጠቅሷል።

#አሚኮ #የቴምር_ፌስቲቫል #ኢትዮጵያ 🇪🇹

#አዲስ_አበባ #መስከረም_07_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሕዝብ ሀብት ኾኖ ይቀጥላል” ሼኽ መሃመድ ሁሴን አሊ አል_አሙዲን
Next articleሜሪቶክራሲ መጽሐፍ ለሀገር ግንባታ እና ለማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው።