“ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሕዝብ ሀብት ኾኖ ይቀጥላል” ሼኽ መሃመድ ሁሴን አሊ አል_አሙዲን

4

 

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የ2018 በጀት አፈፃፀሙን ገምግሟል። ካምፓኒው እንደ ሀገር 390 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኘቱን ገልጿል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ50 በመቶ ጭማሪ ያለው መኾኑ ተጠቅሷል።

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የፕላኒንግ ዳይሬክተር አክሊሉ ሙሉጌታ፣ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አሠራሮችን በማዘመንና ተጨማሪ የሥራ እድሎችን በመፍጠር ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መኾኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ ለግብርና ለሌሎች መንግሥታዊ አገልግሎቶች ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደረገ ሲኾን ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ62 በመቶ በላይ አፈጻጸም እንዳለዉ ተገልጿል።

በማኅበራዊ አገልግሎትም በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በገንዘብና በአይነት የተሰጡ የተለያዩ የማኅበራዊ ድጋፍ ሥራዎች ማከናወኑ ተጠቅሷል፡፡

የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ መሥራችና ባለቤት ሼክ ሙሀመድ ሁሴን አሊ አል_አሙዲን በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት የኩባንያው ስኬት አስደሳች መኾኑን ገልጸው የኢትዮጵያን እድገት ለማሳካት እንሠራለን ብለዋል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሕዝብ ሀብት ነው ያሉት ሼኽ ሙሃመድ ሁሴን አሊ አል_አሙዲን ወደ ፊት የበለፀጉና እንደ G 7 ያሉ ሀገራት ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰበሰቡ እጥራለሁ፣ ይህን ከመላው የሚድሮክ ግሩፕ ጋር ኾነን ለስኬት በማብቃት የኢትዮጵያ ጠላቶች እናሳፍራለን ነው ያሉት።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በስድስት ዘርፎች የተደራጁ ከ45 በላይ የሚኾኑ ድርጅቶችን በስሩ ያቀፈ ነው። በአሁኑ ወቅት 80 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ግዙፍ ኩባንያ ሲኾን ከትርፉ 10 በመቶውን ለማኅበራዊ ኃላፊነት በመመደብ ሀገራዊ ግዴታውን እየተወጣ የሚገኝ የሀገር ሀብት መኾኑም ተገልጿል።

በዕቅድ አፈፃፀሙ የታዩ ስኬቶችን በቀጣይ ለማስቀጠል እንዲያስችለው ለሠራተኞቹ ዕውቅና እና ማበረታቻ ሰጥቷል።

​#ሚድሮክኢንቨስትመንትግሩፕ #ማኅበራዊኃላፊነት #የሥራዕድል

ዘጋቢ: ሃብቴ ተሻገር

#ባሕር_ዳር፡ መስከረም 07/2019 ዓ.ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከባሕር ዳር ከተማ ጋር!
Next articleየቴምር ፌስቲቫል በኢትዮጵያ!