🕊️ ከአፈሙዝ ጩኸት ወደ አዕምሮ ከፍታ – የዕውነተኛ ጀግንነት ምልክት

63

 

ማንኛውም የትጥቅ ትግል መነሻው የቱንም ያህል ፍትሐዊ እና የህልውና ጉዳይ ቢኾንም ጊዜው ሲረዝም እና መልክ ሲቀይር ራሱ የተነሳለትን ማኅበረሰብ የሚበላ የውስጥ ነቀርሳ መኾኑ አይቀርም። በአማራ ክልል አሁንም ድረስ የዘለቀው ግጭት የክልሉን ሕዝብ ለሰላም እጦት እና ለኢኮኖሚ ድቅቀት ዳርጎት ቆይቷል።

የታጠቁ ኃይሎች የጠመንጃ አፈሙዝ የቱንም ያህል ቢጮህ የሕዝብን የዕለት ተዕለት የሰላም፣ የዳቦ እና የነጻነት ጥማት ሊያረካ አይችልም። ዕውነተኛው የዘመኑ የጀግንነት መለኪያ በጦር ሜዳ ጠላትን መጣል ብቻ አይደለም፤ ከራስ አልፎ ትውልድን ከሚያወድም የጥፋት መንገድ ላይ በድፍረት ተመልሶ የሰላምን አማራጭ መቀበል እንጂ።

በጦርነት ውስጥ ፍጹም አሸናፊ የሚባል ነገር እንደሌለ በጦርነት ያለፉ ሀገራት ታሪክ ሕያው ምስክር ነው፤ ያለው አንጻራዊ የኪሳራ መጠን ልዩነት ብቻ እንጂ። የታጠቁ ኅይሎች የክልሉን ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ስብራት በጥልቀት ቢመረምሩ ትግሉ ሳያውቁት የክልሉን አርሶ አደር ከማሳው፣ ነጋዴውን ከገበያው፣ ወጣቱን ከወደፊቱ ራዕዩ እያፋታው መኾኑን ይረዳሉ።

መሳርያን አስቀምጦ የነገን የተሻለች ሀገር በድርድር ጠረጴዛ ላይ ለመገንባት መወሰን የላቀ ሥነ-ልቦናዊ ልዕልናን ይጠይቃል። ይህ የሰላም መንገድ እጅ መስጠት ሳይኾን የሕዝብን ህልውና ከመዋቅራዊ ውድቀት መታደግ ነው።

የትግል ስልትን ከጥይት ድምጽ ወደ ሀሳብ ልውውጥ፣ ከማፍረስ ወደ መገንባት ማሸጋገር፣ የሕዝብን ስቃይ በማሳጠር ረገድ ከምንም በላይ ትልቁ ታሪካዊ ድል ነው።

ዛሬ ላይ ክልሉ የሚፈልገው ጫካ ገብቶ ሕይወት የሚገብር ወጣት ሳይኾን ችግሮችን በበሰለ አካሄድ የሚፈታ፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ እና በኢኮኖሚ ፈጠራ ክልሉን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርለትን ራዕይ የሰነቀ ትውልድን ነው።

የታጠቁ ኅይሎች የሰላምን በር ማንኳኳት የራሳቸውን ማኅበረሰብ ከተደራራቢ ሞት የመታደግ ብቸኛ የነፍስ አድን እርምጃ መኾኑን ሊቀበሉ ይገባል። የፖለቲካ ጥያቄዎችን በጠመንጃ ቋንቋ ለመፍታት የሚደረገው ማለቂያ የሌለው ሙከራ በመጨረሻው ሕገ-ወጥነትን በማስፋፋት ንጹሃን ዜጎች በእገታ እና በዝርፊያ ሰለባ እንዲኾኑ ሰፊ ክፍተት ፈጥሯል።

የግጭቱ ጊዜ አብቅቶ የአማራ ክልል ወጣት እንደፈለገ የሚሠራበት፣ አምራቹ ምርቱን በነጻነት የሚያንቀሳቅስበት እና ማኅበራዊ ትስስሩ ዳግም የሚያብብበት የሰላም ጸደይ እንዲመጣ እና መሳርያን በሃሳብ የማሸነፍ ዘመን ላይ መድረሳችንን ማመን ግድ ይላል።

የጠመንጃ መንገድ ለሀገርም ኾነ ለሕዝብ መከራን ከማትረፍ ባለፈ አንዳች ፋይዳ እንደሌለው እና እርሳቸውም ይህንን ጫካ ገብተው በቅርበት እንዳዩት ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባው ገልጸዋል። ታጥቀው ጫካ የገቡ ኅይሎች የትጥቅ ትግል ከንቱነትን ተረድተው፣ የጥፋትን መንገድ በመተው ጥያቄያቸውን በውይይት፣ በንግግር እና በምክክር መድረክ ብቻ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል።

የክልሉ ነዋሪዎችም ዛሬ ላይ የተገኘው ሰላም ወደ ኋላ እንዳይመለስ ፍላጎታቸው እንደኾነ እየተማጸኑ ነው። በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት ግለሰብ የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት ከቦታ ቦታ የሚደረገው እንቅስቃሴ በአንጻራዊነት መሻሻል አሳይቷል ነው ያሉት። ይህንን ለማስቀጠል ግን እርሳቸውን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ በትጥቅ ላይ ያሉ ወገኖች እና ሌሎችም ወገኖች ኀላፊነት ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ብሩህ እና ሰላማዊ ማኅበረሰብ የሚገነባው ዛሬ ላይ በምናሳየው የሰላም ጥበብ እና የህሊና ከፍታ በመኾኑ ጦርነትን ታሪክ አድርጎ የሰላምን አየር መተንፈስ ብቸኛው የትውልድ መሻገሪያ ድልድይ ነው።

#Ameco #peace #Amhara #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_11_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleዓይነ ሥውሩ የቧንቧ እና የቴክኒክ መሣሪያዎች ጠጋኝ
Next articleየመረጃ ቋት ለምን ይጠቅማል?