
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት በሉዓላዊነት፣ በኢኮኖሚ ጥገኝነት እና በወታደራዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ተጋላጭነትን የሚፈጥር እና ለዘርፈ ብዙ የጂኦ-ፖለቲካዊ እና የስትራቴጂክ አደጋዎች የሚዳርግ ነው።
ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ጥገኛ መኾን ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪን ያስከትላል። ከዚህም በላይ የወደብ ታሪፍ ጭማሪ እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲያጋጥም የውጭ ንግድ እንቅስቃሴን በማስተጓጎል የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ እና የሀገር ውስጥ ገበያ መረበሽን ያስከትላል።
የባሕር በር ማጣት የንግድ ደኅንነትን በሌሎች በጎ ፈቃድ ላይ እንዲመሠረት በማድረግ በችግር ጊዜ የኢኮኖሚ እና የሰላም ሉዓላዊነትን ለአደጋ ያጋልጣል።
እንደ ስዊዘርላንድ እና ኦስትሪያ ያሉ ሀገራት በኮቪድ ወረርሽኝ እና በዩክሬን ጦርነት ወቅት የገጠሟቸው የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጦች ለዚህ አሳማኝ ማሳያዎች ናቸው። ከወታደራዊ እና ስትራቴጂክ ደኅንነት አኳያም ሁኔታው አሳሳቢ ነው።
የሥራ አመራር አማካሪ እና ፖለቲከኛው ጌትዬ ትርፌ (ዶ.ር) እንደሚሉት የባሕር በር ማጣት ወታደራዊ ትጥቆችን እና ስትራቴጂካዊ ንብረቶችን በሦሥተኛ ወገን በኩል ለማስገባት በማስገደዱ፣ የሀገርን ሚስጥሮች ለውጭ አካላት እና ለተቀናቃኞች በማጋለጥ ለከፍተኛ የደኅንነት ተጋላጭነት ይዳርጋል።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በነበረው የዚያን ዘመን ጦርነት ወቅት በሀገሪቱ ላይ የተጣለው ወታደራዊ ማዕቀብ እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያሉት እንቅስቃሴዎች በሦሥተኛ ወገን ፍቃድ ላይ የተመሠረቱ ስለነበሩ ወታደራዊ እና ሀገራዊ ሚስጥሮች በቀላሉ ሲጋለጡ መቆየታቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
የባሕር ኀይል ባለቤት አለመኾንም በጂኦ-ፖለቲካዊ አሰላለፍ ውስጥ የሀገሪቱን ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚገድብ፣ በቀይ ባሕር እና ኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጥተኛ ወታደራዊ እና ሎጂስቲካዊ ተሳትፎ እንዳይኖራት ያደርጋል።
ይህ ሁኔታም በድንበር አቋራጭ ጸረ-ሽብርተኝነት እና በባሕር ደኅንነት ሥራዎች ላይ የሌሎችን መልካም ፈቃድ ብቻ ተስፋ እንድታደርግ ያስገድዳታል።
የባሕር በር ማጣት ኢትዮጵያን በጂኦ-ፖለቲካዊ ጨዋታዎች ከአጥቂነት ይልቅ ተከላካይ እንድትኾን በማድረግ የውጭ ኀይሎች የንግድ ፍሰቷን እንደ መሣሪያ እንዲጠቀሙበት ዕድል ይሰጣል። ይህ የውጭ ጥገኝነት የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነፃነት በማጣበብ ለቀጣናዊ ግጭት እና ለህልውና አደጋ ይዳርጋል።
የባሕር በር ማጣት የኢኮኖሚ አቅምን ከማዳከም ባለፈ ሉዓላዊነትን ለውጭ አካላት አጋልጦ የሚሰጥ የህልውና አደጋ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት የፈጠረባትን ስትራቴጂካዊ ክፍተት በመገንዘብ የኢኮኖሚ እና የወታደራዊ ነፃነቷን ለማረጋገጥ የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግን መሠረት በማድረግ ወደ ቀድሞ የባሕር በር ባለቤትነቷ ለመመለስ እየሠራች ነው።
#Ethiopian_Red_Sea_Access #National_Sovereignty#AMECO
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
