
አቶ መለሰ ጌታነህ ይባለሉ። የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ናቸው። የ62 ዓመቱ አቶ መለሰ በ2002 ዓ.ም በድንገት የሁለት ዐይኖቻቸውን ብርሃን ቢያጡም የዳበሳ ጥበባቸውን በመጠቀም የተበላሹ የቧንቧ እና የቴክኒክ መሣሪያዎችን በመጠገን አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ።
ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በቧንቧ ሙያ ላይ የተሰማሩት አቶ መለሰ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ በተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል የውኃ መስመር በመዘርጋት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል።
የዐይን ብርሃናቸውን ካጡ በኋላ ለአጭር ጊዜ ከቤት ውለው የነበረ ቢኾንም የቀድሞው የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ዓለማየሁ ትኩ ባደረጉላቸው ድጋፍ እና በቤተሰቦቻቸው እርዳታ ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል።
ባለሙያው የሆስፒታሉን የውኃ መስመር ዝርጋታ ካርታ በአዕምሯቸው በመያዝ በዳበሳ ብቻ በመለየት የቧንቧ ዕቃዎችን ጥገና ያከናውናሉ።
በተጨማሪም በሬዲዮ በሚከታተሏቸው ትምህርቶች እና ባለሙያዎችን በስልክ በመጠየቅ ለዓመታት ተበላሽተው የነበሩ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖችን፣ የውኃ መስመሮችን እና የኤሌክትሪክ ምጣዶችን በብቃት መጠገን ችለዋል።
አቶ መለሰ አሁንም በኮንዶሚኒየም ፎቆች ላይ እየወጡ በግለሰብ ቤቶች እና ድርጅቶች የቧንቧ ጥገና በመሥራት ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን በጥሩ ሁኔታ እንደሚያሥተዳድሩ ገልጸዋል።
ወጣቶችም ሥራ ሳይንቁ ከትንሽ ተነስተው ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ትልቅ ደረጃ መድረስ እንዳለባቸው መክረዋል።
አባቱን ተከተሎ በቧንቧ ሙያ ላይ የተሰማራው ወጣት አማኑኤል መለሰ ከአባቱ ጎን በመቆም የቴክኒክ ዕውቀቱን ከመቅሰሙ ባለፈ በማንኛውም ፈተና ውስጥ ተስፋ አለመቁረጥን እና የጽናትን ትርጉም በተግባር መማሩን ገልጿል።
የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል የግዥ እና ፋይናንስ ቡድን አስተባባሪ አሰፉ ምትኩ አቶ መለሰ በሥራቸው እጅግ ምስጉን እና ትጉህ ሙያተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የገጠማቸውን ፈተና በጽናት ተቋቁመው የሚያከናውኑት አገልግሎት ሙሉ አካል እያላቸው ሥራቸውን በአግባቡ ለማይወጡ ሰዎች ትልቅ የሕይወት ትምህርት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
#Ameco #ጽናት_እና_አርዓያነት
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_11_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
