
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና እና ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት በ2018 በጀት ዓመት በካፒታል ፕሮጀክት ያስገነባቸውን መማሪያ ክፍሎች አስመርቋል።
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ምግብ ዋስትና እና ልማታዊ ሴፍቲኔት ሥራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እመቤት መንግሥቱ መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር ባደረገው ስምምነት እና በተገኘው በጀት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ዜጎች ኑሮ ከማሻሻል ባሻገር ለከተማዋ ማኅበረሰብ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ለመገንባት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በከተማዋ በ2018 በጀት ዓመት ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ የካፒታል በጀት በሦሥት ትምህርት ቤቶች 20 የመማሪያ ክፍሎች ያሏቸው አምስት ብሎኮች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሀገሩን የሚወድ፤ ለሀገሩ ልማት እና ብልጽግና አቅዶ የሚሠራ ትውልድ የሚገነባው በትምህርት መኾኑን ተናግረዋል። ትምህርት ለሀገር ልማት እና ዕድገት የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል። ይህን ለማድረግ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት።
በባሕርዳር ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ከተማዋን የሚመጥኑ አድርጎ ደረጃቸውን ማሻሻል ያስፈልጋልም ብለዋል። ይህን ለማድረግም በከተማ አሥተዳደሩ በጀት፣ በአጋር አካላት ድጋፍ እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በከፍተኛ በጀት ደረጃቸው የተሻሻለላቸው እና የተገነቡ ትምህርት ቤቶች እንዳሉም ጠቅሰዋል። የቀሪ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
የ2018 በጀት ዓመት የካፒታል በጀትን የሕዝብን ችግር በሚቀርፉ ተግባራት ላይ ማዋል እንደተቻለ ተናግረዋል።
በከተማዋ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ባሻገር የኦቲዝም ተጠቂ ሕጻናት መማሪያ ትምህርት ቤት እንደሚገነባም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) ሀገር አቀፍ በኾነው የከተሞች ምግብ ዋስትና እና ልማታዊ ሴፍትኔት መርሐግብር በአማራ ክልል 606 ሺህ እና በባሕር ዳር ከተማ ደግሞ 50 ሺህ የሚኾን ሕዝብን ተጠቃሚ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
መርሐግብሩ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ በትኩረት እየተሠራበት ነው ብለዋል። በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ90 በላይ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን ተናግረዋል። በሚቀጥሉት ዓመታትም የትምህርት ተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።
የትምህርት ቤት ግንባታ ለልብ የቀረበ ወሳኝ ሥራ ነው ያሉት ኀላፊው በባሕር ዳር ከተማ ሕጻናት በምቹ ሁኔታ ውስጥ ኾነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማስቻል የተከናወነው ግንባታ የሚመሠገን ነው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ በግንባታው አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
#Ameco #SchoolBulding #Bahirdar #Amhara
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_11_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
