
ጦርነት ሁልጊዜም ከባድ የሕይወት መስዋዕትነት ያስከፍላል፤ ከቁሳዊ ውድመት በላይ ደግሞ የሰዎችን ህሊና እና የማኅበረሰብ እሴትን ይሸረሽራል።
በአማራ ክልል ላለፉት ሦስት ዓመታት የዘለቀው የጸጥታ ችግር የወለደው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድመት የዚሁ መራራ እውነት ማሳያ ነው።
ይሁን እንጂ በማወቅም ኾነ ባለማወቅ በዚህ ትርጉም የለሽ ጦርነት ሲሳተፉ የነበሩ ወጣቶች ያለፈውን ጥፋት በቁጭት እና በፀፀት እየገመገሙ ወደ ሰላማዊ ሕይወት በመመለስ ላይ ይገኛሉ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ተሳትፎ የነበረው ወጣት ይካስ ዘነበ የተዘረጋለትን የሰላም አማራጭ ተቀብሎ ወደ ኅብረተሰቡ መቀላቀሉን ገልጿል። ትግሉ ከተጀመረበት ዓላማ ወጥቶ የግል ሀብት ማካበቻ መኾኑን ወጣት ይካስ ተናግሯል።
“ይህ ሕዝብ ትናንት የውጭ ጠላት ሀገራችንን ሊደፍር በመጣ ጊዜ በአንድነት ቆሞ ሀገርን ከወራሪ ታድጓል፤ ሀገር አቅንቶ እና አጽንቶ በክብር ለትውልድ አስረክቧል። ፍቅር እና ደግነትን አስተምሮ ያሳደገን ታላቅ ሕዝብ ነው፤ ሕዝባችንስ መልካም ነበር፤ እኛ ልጆቹ በደልነው እንጂ” በማለት የወገኑን ውለታ እና ያለፈውን ጥፋት በቁጭት አንስቷል።
የሰላም አማራጭን የተቀበለው ሌላኛው ጌታሰው ዮሴፍ “የሕዝብን ጥያቄ እናስመልሳለን” በሚል መነሻ የተጀመረው የትጥቅ እንቅስቃሴ ሕዝብ ላይ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ እያደረሰ መኾኑን በትግል ወቅት ማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል።
በግጭቱ ምክንያት ሕዝብ እየተበደለ ነው። ለምግብ እና ለትጥቅ ማሟያ በሚል ደሃ እና ሀብታም እኩል የገንዘብ ወጭ እየተጠየቀ ነው። ሕዝቡም የተጣለበትን የገንዘብ መዋጮ ተገዶ እየከፈለ ነው ይላል። እኛ በፈጠርነው ጦርነት ከታጋዩ ይልቅ ንጹሐኑ እና ሰላማዊው ሕዝብ እየሞተ ነው በማለት መሬት ላይ ያለውን እውነታ በቁጭት ተናግሯል።
ለዘመናት በወንድማማችነት እና በደግነት የጸናው ሕዝባቸው ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ ጫካ የገቡ ኃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱም ወጣቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሰሞኑ ባስተላለፉት መልዕክት የጦርነትን አውዳሚነት በመገንዘብ በየጊዜው በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ መርጠው ወደ ኅብረተሰቡ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ ማለታቸው ይታወሳል።
መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ያልተለወጠ መኾኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንኛውም አካል በሰላማዊ መንገድ ሀሳቡን ይዞ ለመታገል እስከፈለገ ድረስ የመንግሥት የሰላም በር መቼም ቢሆን እንደማይዘጋ አረጋግጠዋል።
#አሚኮ #peace #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_11_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
