የምክክር ሀሳቦችን የማጣጣም እና የማጠናቀቅ ሥራ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል።

20

 

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለው ሲካሄዱ የቆዩ የምክክር ሀሳቦችን የማጣጣም እና የማጠናቀቅ ሥራ ተጠናቅቆ ለሁሉም ተሳታፊዎች ሊቀርብ መኾኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ ሥላሴ ተናግረዋል።

ላለፉት ቀናት ሲከናወን የቆየው የማጣጣም ሥራ በስምንቱ ቡድኖች በቀረቡ የምክክሩ ሀሳቦች መካከል ድግግሞሽ እና ተቃርኖ እንዳይኖር ሰነዱ አንድ ወጥ በኾነ መልክ እንዲዘጋጅ ለማስቻል የተከናወነ ወሳኝ ምዕራፍ እንደኾነም ጠቅሰዋል።

በሂደቱ ዙሪያ የነበሩ ዋና ዋና ነጥቦችን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሯ የግብዓት የመሠብሠብ ምዕራፍ አንዱ እንደኾነ አንስተዋል። የተጣጣሙት የምክክሩ ሀሳቦች ለሁሉም ስምንት ቡድኖች መልሰው እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎች ቀደም ሲል ባልተሳተፉባቸው ሌሎች ሰባት ቡድኖች ሥራዎች ላይ ተወያይተው ግብዓት ይሰጣሉም ብለዋል።

ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ የሚሠበሠበው ግብዓት ተጠቃልሎ ነገ በሚከናወኑ ሥራዎች ከዳበረ በኋላ በዕለተ ረቡዕ ከ4ሺህ በላይ በሚኾኑ ሙሉ የጉባኤው ተሳታፊዎች ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በሂደቱ ላይ ለተነሱ ቅሬታዎች ምላሽ የሚሰጥ ልዩ ኮሚቴ የተቋቋመ መኾኑንም አንስተዋል። ኮሚቴው የሚያቀርባቸውን ግኝቶች መሠረት በማድረግም የኮሚሽነሮች ካውንስል ውሳኔ እየሰጠ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ጉባኤው በአብዛኞቹ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ መግባባት ላይ መድረሱንም ገልጸዋል። ይህም ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና መግባባት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

በጉባኤው ላይ ሁሉንም የኢትዮጵያ ወረዳዎች እና ባለድርሻ አካላት የሚወክሉ ተሳታፊዎች በስምንቱም ቡድኖች ውስጥ ተከፋፍለው በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

#አሚኮ #ምክክር #ኢትዮጵያ

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_11_2018_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየባሕር በር ማግኘት የሕልውና ጉዳይ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
Next article“ሕዝባችንስ መልካም ነበር፤ እኛ ልጆቹ በደልነው እንጂ” የቀድሞ ታጣቂዎች