
የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ወሳኝ የሕልውና ጉዳይ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ ወጣቶች ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡት ወጣት ቴዎድሮስ ተስፋዬ እና ወጣት ወሩ ነጋሽ የባሕር በር አለመኖር የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል በዜጎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አብራርተዋል።
ወጣት ቴዎድሮስ “የባሕር በር ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ መፍጠር እንጂ ያለ ባሕር በር ተዘግቶ መኖር አይገባም” ብሏል። በሰላማዊ እና በጋራ ተጠቃሚነት አካሄድ የባሕር በር ማግኘት እንደሚገባ ጠቁሟል።
የባሕር በር ባለቤት መኾን በዚህ ዘመን ግዴታ ሊኾን እንደሚገባም ገልጿል።
ወጣት ወሩ በበኩሉ “ኢትዮጵያ በድህነት ተዘግታ መኖር የለባትም፤ ለቀጣዩም ትውልድ ድህነትን ማስተላለፍ የለብንም” ብሏል። ጥያቄው በዲፕሎማሲ እና በውይይት ምላሽ እንዲያገኝ መሥራት ይገባል ነው ያለው።
ኢትዮጵያ ከባሕር በር ርቃ መኖር እንደሌለባት የገለጹት ወጣት መለሰ ዓለሙ እና ወጣት ወረቅነሽ ፀጋ የባሕር በር ጥያቄ የመላው ሕዝብ የጋራ አጀንዳ መኾኑን አንስተዋል።
ወጣት መለሰ ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ማሳለጫ በመኾን የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ገልጿል።
ወጣት ወረቅነሽ ፀጋ በበኩሏ ጉዳዩን በውይይት እና ሀሳብን በማስቀደም መፍታት እንደሚገባ ገልጻለች። ጥያቄው ሲመለስ ሀገሪቱ ለሌሎች ተምሳሌት መኾን የምትችልበት መንገድ እንደሚፈጠር ተናግራለች።
#አሚኮ #የባሕርበር #ኢትዮጵያ
#ደብረ_ታቦር #ነሐሴ_11_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
