
ወርሐ ነሐሴ ምድር በልምላሜ የምትሞላበት እና የአዲስ ዓመት መምጣት በጉጉት የሚጠበቅበት ወቅት ነው። በምዕራብ ጎጃም እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የእንግጫ ነቀላ እና ከሰይ አጨዳ በዓል በልዩ ድምቀት ይከበራል።
ወጣቶች እና ልጃገረዶች በዓሉን በተለያዩ ባሕላዊ አልባሳት እና አጊያጊያጥ ተውበው ደምቀው የሚያከብሩበት ሁነትም ነው።
አሚኮ ያነጋገራቸው የበዓሉ ተጫዋቾች እንግጫ፣ ሙርኝ እና አጥምቢላ የሚባሉ የሳር ዓይነቶችን በመንቀል እና በማዘጋጀት የተለያዩ ዜማዎችን በመጫወት የሚያከብሩት በዓል መኾኑን አስረድተዋል።
ተጫዋቾቹ ”የቅዱስ ዮሐንስ ያላሰረች ቆንጆ
ቁማ ትቀራለች እንደ ወፍ ጎጆ” በማለት ወንዶች ስንኞችን በመምዘዝ ለማጨት የሚፈልጓትን ልጃገረድ ፍላጎታቸውንም ጭምር የሚገልጹበት ዕለትም መኾኑን ይገልጻሉ።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴት ልማት ቡድን መሪ አበቡ መኩሪያው እንግጫ የአዲስ ዓመት የልምላሜ ምልክት መገለጫ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይ ሰፊ ጥናቶችን በማካሄድ በዓሉ ከባሕል እሴትነቱ ባሻገር ማኅበራዊ ፋይዳውንም ጭምር አጉልቶ ለትውልድ ማሻገር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ የኔነሽ አስቻለ የእንግጫ ነቀላ በዓል በጃቢ ጠህናን፣ ቡሬ ዙሪያ እና ወምበርማ ወረዳዎች በስፋት የሚከበር ዓመታትን የተሻገረ ባሕል መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም ”ባሕል ድልድያችን፣ የአንድነት መዳረሻችን” በሚል መሪ መልዕክት በሕሉን እና ትውፊቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲሻገር በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በዓሉ ከነሐሴ 21/2018 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳዎች በድምቀት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
#አሚኮ #የእንግጫነቀላ #ከሰይ አጨዳ #ምዕራብጎጃም_አማራ_ክልል
#ፍኖተ_ሰላም #ነሐሴ_11_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ንጉሥ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
