
ከሰሞኑ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ወደ አለ አንድ የጤና ጣቢያ አቅንቼ ነበር። ጤና ጣቢያው ለማረፊያ ባዘጋጀው አግዳሚ ወንበሮች ላይ ሕሙማን ተሰድረዋል።
በጤና ጣብያው ተቀምጠን ሳለ ሰዎች አንድ በመካከለኛ ዕድሜ ውስጥ ያለ ታማሚ ይዘው መጡ። ልጁ ከሕመሙ ጽናት የተነሳ ያቃስታል። እኛም ታማሚው ምህረት እንዲሰጠው ለፈጣሪ እየተመኘን ምን እንደገጠመው ጠየቅን።
በዕድሜ ገፍ ያሉ እናቱ ስለጉዳዩ ሲያጫውቱን ልጁ ሲታመም የሚታይበትን ምልክት በማየት ጎረቤት ዘመዱ የወፍ በሽታ እንደኾነ እና ወደ ባሕል ሕክምና እንድንወስደው ግፊት ሲፈጠር እኛም ወደ ባሕል ሕክምና ወሰድነው ይላሉ።
የባሕል ሐኪሙ ምላሱን ገልብጠው በምላጭ በጡት። ነገር ግን ከሕመሙ መዳን አልቻለም። በዚህ ምክንያት ወደ ዘመናዊ ሕክምና ይዘውት ሄዱ። ልጃቸው በቀላሉ ታክሞ በሚድንበት ጊዜ ወደ ሕክምና ባለመውሰዳቸው ለበለጠ ችግር መዳረጋቸውን አይተን አዘንን።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አዕምሮየ ላይ የሚመላለሰው ጉዳይ ለመኾኑ የወፍ የሚባል በሽታ አለ? የሚል ኾነ።
ይህንንም ጥያቄየን እንዲመልሱልኝ ወደ በአማራ ክልል የባሕል ሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት ሊቀጠበብት እምወደው አዘዘ ደወልኩላቸው። የባሕል ሐኪሙም ሲመልሱ የወፍ በሽታ የሚባለው በዘመናዊው የጉበት በሽታ እንደኾነ እና በዕጽዋት መልክ የሚሰጥ መድኃኒት እንዳለው ነገሩኝ። ይሁን እንጅ የባሕል ሕክምና በዕጽዋት የሚቀመም አለበለዚያም ከእንሰሳት ተዋጽኦ እና ከማዕድናት የሚዘጋጁ መድኃኒቶች ካልኾኑ በስተቀር በሰዎች አካል ላይ በስለት የሚከናወን የባሕል ሕክምና እንደሌለ እና አጥብቀው እንደሚያወግዙት ተናግረዋል።
በምላስ ስር መብጣትን ጨሞሮ በአካል መቁረጥ የሚከናወን ሕክምናን ለማስቆም ማኅበሩ እየሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና መምህርቷ ዶክተር እስከዳር ሞላ ጉዳዩ ማኅበረሰባችንን እየጎዳ ያለ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ የወፍ በሽታ እያለ የሚጠራው የጉበት ወይንም በሕክምና አጠራሩ የሂፓታይተስ በሽታን ነው ይላሉ።
በሕክምናው ዘርፍም ብዙ እያነጋገረ ያለ እና ማኅበረሰቡም በተሳሳተ መንገድ እየሄደ ጉዳት እየደረሰበት መኾኑን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ የወፍ በሽታ የሚለው ከሚያያቸው ምልክቶች ተነስቶ እንደኾነ የተናገሩት ዶክተሯ በተለይም ዐይናቸው ቢጫ የኾነ፣ የሚያስታውካቸውን ሰዎች፣ ሆዳቸውን የሚያማቸውን ሰዎች እና መሰል ምልክቶችን በማየት ብቻ የወፍ በሽታ እያለ እንደሚጠራው ነው የተናገሩት።
ዶክተር እስከዳር እንደሚሉት ግን የወፍ በሽታ የሚባል በሕክምና የለም። ማኅበረሰቡ መገንዘብ ያለበት ሰዎች ዐይናቸው ቢጫ የሚኾነው በሰውነት ውስጥ ያለ ያረጀ የደም ሴል ሲጨምር ነው ብለዋል። ይህ እንዲጨምር ብዙ ምክንያቶች እንዳሉም ተናግረዋል።
የደም ሴሎችን የሚጎዳ በሽታ ሲኖር፣ በተለይ ቀይ የደም ሴሎች እንደ ወባ እና መሰል የደም ሴሉን የሚጎዱ ነገሮች ሲኖሩ ዐይን ቢጫ ሊኾን ይችላል ነው ያሉት።
ሌላው ጉበት ላይ ችግር ሲኖር ይፈጠራል ነው ያሉት። ያረጁ የደም ሴሎች የሚያስወጣው ጉበት ስለኾነ ያንን ማድረግ በማይችልበት ጊዜ በቫይረስ ሲጠቃ፣ በአልኮል እና በተለያዩ ምክንያቶች ጉበት ሲጎዳ የዐይን ቢጫ መኾን ሊያመጣ እንደሚችል ተናግረዋል።
ምንም እንኳን የወፍ በሽታ የሚባል በሕክምናው ባይኖርም አንዳንድ የግል ተቋማት የወፍ በሽታ ምርመራ እናደርጋለን እያሉ እንደሚያክሙ ገልጸዋል። ይህም ስህተት ነው ብለዋል።
የባሕል ሕክምና ሙሉ ለሙሉ ችግር አለበት ተብሎ አይወሰድም ያሉት ዶክተሯ ነገር ግን ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ብሎም በመድኃኒት ሊድኑ የሚችሉ በሽታዎች ጊዜ በመውሰድ ብዙ ተያያዥ ችግሮች ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት።
ሰዎችን በባሕል ሕክምና ሰበብ ተደርጎ ከፍተኛ ጉዳት ላይ የሚጥሉ ምላስ ላይ መብጣት ከዚያም ከበድ ባለ መንገድ ምንነቱ ያልታወቀ ፈሳሽ ነገር ሰጥተው እንዲጠጡ በማድረግ ጉዳት እያስከተሉ እንደኾነም ነው የጠቆሙት። ብዙ ሰዎች በእንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ ገብተው ለሕክምና መጥተው ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።
ሰዎች አሁን የወፍ በሽታ እያሉ የሚለዩበት ምልክት የተለያዩ በሽታዎች ምልክት መኾኑን ኅብረተሰቡ ተረድቶ ጉዳት ላይ ከመውደቁ በፊት ራሱን መጠበቅ ይገባዋል ነው ያሉት።
ባሕላዊው ሕክምና ከዘመናዊው ጋር ተጣምሮ በጥናት እየተደገፈ እና አንዱ የማይሞላውን ክፍተት ሌላው እየሞላ ወደፊት ሊቀጥል የሚችል ዘርፍ እንደኾነም ገልጸዋል።
ነገር ግን ይህን ዘርፍ በትክክል ያልተረዱ ሰዎች እናክማለን ስለሚሉ ዘርፉ ጉዳት እንዲያስከትል እያደረገው እንደኾነም ጠቁመዋል።
የባሕል ሕክምና የሚሰጡ ሰዎችም ከዘመናዊው ሕክምና ጋር ተመካክረው ቢሠሩ እና ትብብር ቢዳብር ሕዝብንም ኾነ ራስን መጥቀም እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት።
#AMECO #HepatitisAwareness
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_11_2018_ዓ_ም
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
