
የአማራ ክልል ፕላን ኢንስቲትዩት ያለፈውን በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የቀጣይ ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እያካሄደ ነው።
በተጨማሪም በፕላን አተገባበር የሕግ ማዕቀፍ ዙሪያ ለዞን፣ ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እና ለከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች እና ባለሙያዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው።
የአማራ ክልል ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ምትኩ ዓለማየሁ (ዶ.ር) እንዳብራሩት የከተማ ፕላን ለኢኮኖሚ ሽግግር እና ለነዋሪዎች ምቹ የኑሮ አካባቢን ለመፍጠር ወሳኝ ነው።
ፕላን በአስተማማኝ መረጃ ላይ ተመስርቶ የሚዘጋጅ ሕግ መኾኑንም ጠቁመዋል። የመሬት አጠቃቀምን፣ የመሠረተ ልማትን፣ የአረንጓዴ ልማትን እና ኢንቨስትመንትን በግልጽ የሚወሰን የከተማ መሠረት ነው ብለዋል።
ከተሞች የ85 በመቶ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ምንጭ መኾናቸውንም ጠቁመዋል። ከተሞች ተገቢው ትኩረት ካልተሰጣቸው እና በፕላን ካልተመሩ የሕገ ወጥ ድርጊቶች ማዕከል ሊኾኑ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ “ሥልጡን ፕላን ለተሻለ ሕይወት” በሚለው መሪ መልዕክቱ የሰዎችን ሕይወት ምቹ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ዘመናዊ ከተማ የሕንጻዎች መደራረብ ብቻ ሳይኾን አገልግሎቶች በፍጥነት የሚደርሱበት፣ የመሬት አሥተዳደሩ የዘመነበት እና የተቀናጀ መሠረተ ልማት ያለው መኾኑ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ፕላን የማዘጋጀት፣ የተዘጋጁ ፕላኖችንም ሕግን ጠብቀው መተግበራቸውን የማረጋገጥ፣ ግድፈቶች ሲገኙ በሕግ ተጠያቂ የማድረግ እና አሠራርን የሚጥሱ የዞኒንግ ለውጦችን የማስቆም ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑንም አስታውቀዋል።
በኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አሠራሩን የሚያጠናክሩ ሦሥት ማኑዋሎች እና መመሪያዎችን ማዘጋጀት ተችሏል ነው ያሉት። እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች ፕላን ሕግ መኾኑን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።
ከገጠር ቀበሌ ስኬች ፕላን እስከ ከፍተኛ መዋቅራዊ ፕላን የሚደርሱ ከ130 በላይ የተለያዩ የፕላን አይነቶችን በማዘጋጀት፤ በ129 ከተሞች ላይ የድጋፍ፣ የኦዲት እና የፕላን ማጽደቅ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት አዲስ የፕላን አዋጅ እና መመሪያዎችን ማዘጋጀት እና ማጸደቅ፤ ከተያዙት 187 የፕላን አይነቶች ውስጥ የ130 የገጠር ቀበሌ ማዕከላት እና የ50 ታዳጊ ከተሞችን ፕላን ለማዘጋጀት መታቀዱን አስታውቀዋል።
በገጠር ቀበሌ ማዕከላት ሥራ ላይ የጸጥታ ችግሩ ፈተና እንዳይኾን ግን የከፍተኛ መሪዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተጠይቋል።
የዞኒንግ ለውጥ ጥያቄዎችን በሕግ ብቻ ማስተናገድ፣ የ30 ከተሞችን ፕሮፋይል ማዘጋጀት፣ ከ60 በላይ ከተሞችን መደገፍ እና የ90 ከተሞች ፕላን በምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግም የዕቅዱ አካል ናቸው።
የፕላን ዝግጅቱንም ዘመናዊ ለማድረግ ከስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሳተላይት ምስል እና የአየር ላይ ፎቶዎችን እንደሚጠቀሙም አስታውቀዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስራቴ ሙጬ ከተሜነት በፍጥነት እያደገ እና እየሰፋ በመምጣቱ ከተሞች በፕላን መመራታቸው ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማም በፍጥነት እያደገች በመምጣቷ በፕላን መመራቷ ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል። በከተማዋ የ30 ዓመት መዋቅራዊ ፕላን በማውጣት ተግባራዊ እየተደረገም ነው ብለዋል።
ለ20 ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች እና የጸጥታ አካላት የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ መዘጋጀቱን የገለጹት ወይዘሮ አስራቴ የከተማዋን የፕላን አተገባበር በማስጠበቅ እና ጥሰትን በመከላከል ረገድም ኢንስቲትዩቱ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መኾኑን አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
