የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ መሠረቶች ናቸው።

4
ፋዊ ኢትዮጵያ ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከክልል ተቋማት እና ከቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ጋር በባሕር ዳር ከተማ እየመከረ ነው።
የፋዌ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሰላማዊት አድማሱ እንደተናገሩት ድርጅቱ ከአጋር የመንግሥት ተቋማት እና ከግል ዘርፉ ጋር በመተባበር ወጣቶች ጥራት ያለው ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ እየሠራ ይገኛል።
በቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት የሚሠጡ ሥልጠናዎች ከኢንዱስትሪ ትሥሥር እና ከቅጥር ፍላጎት ጋር መጣጣም ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። ለዚህ ስኬታማነትም የግል እና የመንግሥት ዘርፉ ቅንጅት ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል።
🏭⚙️
ስኬት የሚለካው ወጣቶች ሥልጠናቸውን በብቃት ተወጥተው በዘላቂ የሥራ ዕድል ሢሠማሩ ነው ብለዋል። ማንኛውም ወጣት በጾታ፣ በአካል ጉዳት እና በማንኛውም የማኅበራዊ ዳራ ከሥልጠና እንዳይገለል መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።♿
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አማረ ዓለሙ የቴክኒክ እና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዋነኛ መሠረቶች ናቸው ብለዋል። አመለካከት በመቀየር እና ክህሎትን በማሳደግ በኩል ኮሌጆች ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ፋዌ ኢትዮጵያ በአማራ ክልልም ከኮሌጆች ጋር በመተባበር በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ዘርፎች ላይ ሥልጠና በመሥጠት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።🔬💻
የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ፈለቀ ውቤ እንደተናገሩት ፋዊ ኢትዮጵያ በኮሌጁ በክህሎት፣ በስርዓተ ጾታ፣ እና በአካታችነት ሥልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
በኮሌጁ በርካታ ሠልጣኞች በፋዌ ተደግፈው እየሠለጠኑ ነው ብለዋል። ለመምህራን እና አሠልጣኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችንም በፋዊ ድጋፍ አማካኝነት መሥጠት መቻሉን አንስተዋል።📈
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ማዕረግ ግዳጅን በላቀ ውጤት በመፈጸም የሚገኝ ክብር” ሜጀር ጀነራል ተስፋዬ ረጋሳ
Next articleከተሞች በፕላን ካልተመሩ የሕገ ወጥ ድርጊቶች ማዕከል ሊኾኑ ይችላሉ።