
የምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ በባሕር ዳር ለሚገኙ የዕዙ ስታፍ አባላት ማዕረግ አልብሰዋል። በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልእክት ማዕረግ እንዲሁ የሚሰጥ ነገር አይደለም፤ ውጣ ውረድ እና ድካም አለው ብለዋል። ግዳጅን በሥነ ምግባር እና በላቀ ውጤት በመፈጸም የሚገኝ ክብር ስለመኾኑም አንስተዋል።
ወታደር ለሀገሩ በሠራው ልክ በየጊዜው የማዕረግ ዕድገት ያገኛል ያሉት ምክትል አዛዡ ዛሬ የተሾሙ ጓዶች የመቆያ ጊዜያቸውን ስለሸፈኑ ብቻ ሳይኾን ለሀገራቸው በጽናት ቆመው ለከፈሉት ዋጋ ማረጋገጫ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
ሜጀር ጄኔራል ተስፋዬ እንዳሉት ሹመቱ ለቀጣይ የበለጠ መሥራት እንደሚችሉ ማሳያ ነው። “ተቋሙ አምኖባችሁ በሰጣችሁ ማዕረግ ጠንክራችሁ በመሥራት የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባችኋል” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
ዛሬ ማዕረግ የለበሱ አባላት ከራሳቸው አልፈው ሌላውን የሚመሩበት ብቃት እንዳላቸው እና በአደራ የተሰጣቸውን ዕድገት በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ምክትል አዛዡ አስገንዝበዋል።
መረጃው የምሥራቅ ዕዝ ነው።
