
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በከሰል እና ተያያዥ ጭሶች አደጋ ምክኒያት 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በዓመት ህይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
ይህ ምግብ ለመዘጋጀት በየቤታችን የምናዘወትሮው ከሰል አጠቃቀሙ ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት የሚያሳይ ነው።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሀኪም ግዛው ሆስፒታል የድንገተኛና የጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስት ዶክተር ሽመልስ ጌታነህ የከሰል ጭስ በውስጡ ‘ካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ’ የተባለ እጅግ አደገኛ ጋዝ ይዟል አሉ። ይህ ገዳይ ጋዝ ወደ ሰውነት በሚገባበት ወቅት በቀጥታ ከደም ስር በመቀላቀል ሕዋሳት የሚያስፈልጋቸውን የኦክስጅን መጠን በከፍተኛ ኹኔታ ያሳጣቸዋል።
በዚህም ምክንያት ተጎጂዎች ሳያውቁት ከቀላል ራስን የማዞርና የመታፈን ስሜት ጀምሮ እስከ ድንገተኛ የሕይወት ህልፈት ለሚደርስ ከባድ አደጋ ይጋለጣሉ።
ጋዙ ምንም ዓይነት ሽታ ወይም የሚታይ ቀለም ስለሌለው በርካታ ሰዎች አደጋው ሲደቀንባቸው ቀድመው አለማወቃቸው ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
በተለይም በቅዝቃዜ ወቅት በርና መስኮት ዘግቶ ከሰል መጠቀም፣ አደጋውን በእጥፍ በመጨመር ቤቶችን ወደ መርዛማ አየር ማከማቻነት ይለውጣቸዋል።
ስለዚህ የከሰል ጭስ አደጋን ቀድሞ ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጽኑ ህሙማን ስፔሻሊስቱ አሳስበዋል።
#ከሰል መጠቀም ግዴታ በሚኾንበት ጊዜም በቤት ውስጥ በቂ የአየር ዝውውር እንዲኖር በርና መስኮቶችን ክፍት ማድረግ ተገቢው መኾኑን ዶክተር ሽመልስ መክረዋል።
#በተጨማሪም ከሰል በመቀጣጠል ላይ እያለና ከፍተኛ ጭስ በሚያወጣበት ወቅት በምንም ዓይነት ኹኔታ ወደ ቤት ውስጥ ማስገባት አደገኛ ነው።
#ችግሩ ተከስቶ ሰዎችን ማፈን ሲጀምርም፣ ተጎጂዎችን በፍጥነት ወደ ውጭ በማውጣት ንጹህ አየር እንዲያገኙ ማድረግ የመጀመሪያው የሕይወት አድናኝ እርምጃ ነው።
#በተጨማሪም የጉዳቱ ሰለባዎችን ያለ ምንም መዘግየት በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ወስዶ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው።
በለአለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
