በቱሪስት ከተማዋ ደባርቅ እየተከናወነ ያለው የልማት ሥራ ለንግድና ለቱሪዝም ዕድገት አዲስ ተስፋ ፈንጥቋል።

4
በደባርቅ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ በማሻሻል ለንግድ እንቅስቃሴ እና ለቱሪዝም ፍሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ጥንታዊቷ ደባርቅ ከልማት ርቃ መቆየቷን ያነሱት የከተማዋ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማቱ የሁሉንም ፍላጎት የሚያሟላ በመኾኑ ማኅበረሰቡ በሀሳብ፣ በጉልበት እና በገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ነዋሪዎቹ በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የታየውን የልማት እና የውበት ለውጥ በደባርቅም ለማየት ተስፋ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት ጸጋየ የቱሪስት መዳረሻ የኾነችውን ደባርቅ ለጎብኝዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የመንገድ ቆረጣ እና ቦታዎችን ከሦሥተኛ ወገን ነፃ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የኮሪደር ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ ነሐሴ 18/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሀብት ማሠባሠብ መርሐግብር እንደሚካሄድ የጠቆሙት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የአካባቢው ተወላጆች፣ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዚህ መርሐግብር ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሻደይ በዓል በሰላም እንዲከበር የጸጥታ መዋቅሩ ዝግጅቱን አጠናቋል።
Next article“የጥንቃቄ ጥሪ”