“መሠረተ ልማትን የኢኮኖሚ ማሳለጫ ሞተር አድርጎ መምራት ይገባል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

3

 

በአማራ ክልል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚያከናውኑ ባለድርሻ ተቋማት በ2018 በጀት ዓመት የጋራ የዕቅድ ግምገማ እና በ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) በዚህ ወቅት እንደተናገሩት መሠረተ ልማት የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት መሠረት ነው። የመሠረተ ልማት ዘርፍ አገልግሎትን የሚያሳልጥ የዛሬ የልማት አሳላጭ የነገ ደግሞ አስቻይ የልማት ዕድል መሠረት ነው ብለዋል።

መሠረተ ልማት መንግሥት ለሕዝብ ቃል ኪዳን የገባቸውን ጉዳዮች ወደ ተጨባጭ አገልግሎት የሚቀይርበት መሳሪያ መኾኑንም ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የሚበረታታ የመሠረተ ልማት አፈጻጸም መመዝገቡንም ገልጸዋል። በመንገድ ጥገና፣ በድልድይ ግንባታዎች ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውንም አንስተዋል። በመጠጥ ውኃም ሽፋኑን መሻሻል ተችሏል ነው ያሉት።

በኤሌክትሪክ ኃይልም በሰብስቴሽን ግንባታዎች፣ በማስተላለፊያ መሥመሮች፣ በመልሶ ጥገና እና በተደራሽነት አበረታች ተግባራት መሠራታቸውን አንስተዋል።

በቴሌ አገልግሎትም በርካታ አዳዲስ ጣብያዎች እንዲከፈቱ በማድረግ እና የኔትወርክ ተደራሽነትን በማስፋፋት በኩል ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት። ይህም ስማርት ከተሞችን የመፍጠር እና ለመጭው ጊዜ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ዝግጁነትን ታሳቢ ተደርገው የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት መኾናቸውን አብራርተዋል።

በመሥኖ ልማት ፕሮጀክቶች የጥናት እና ዲዛይን ሥራዎችም የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል ነው ያሉት። በግንባታ ፕሮጀክቶችም ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ከ7 በላይ ቆመው የነበሩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ማሥገባት ተችሏል ነው ያሉት።

በበጀት ዓመቱ በተሻለ ደረጃ የተከናወኑ የመሠረተ ልማት አፈጻጸሞችን በማበረታታት፣ ክፍተት የታየበትን አፈጻጸም ደግሞ መፈተሽ እና በቆራጥነት ለማስተካከል መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በወረቀት ላይ ብቻ ያለ ዕቅድ ሕዝቡን አይጠቅምም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ሕዝቡ ዕቅድ ብቻ ሳይኾን ውጤትም እንዲያይ እና ተጨባጭ ጥቅም እንዲያገኝ መሥራት አለብን” ነው ያሉት።

በ2019 በጀት ዓመት የመሠረተ ልማት ዘርፍ “ከዕቅድ ወደ ተግባር፣ የቆሙትን ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ማስገባት፣ ከዘገዩ ፕሮጀክቶች ወደ ፍጥነት፣ ከቃል ኪዳን ወደ ተጨባጭ ውጤት” የሚሉ መርሆዎችን በመከተል መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሰላም እና ልማትን አጀንዳነት በመያዝ በቁርጠኝነት መምራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

“መሠረተ ልማትን የኢኮኖሚ ማሳለጫ ሞተር አድርጎ መምራት ይገባል” ብለዋል። መንገድን፣ መሥኖን፣ ኤሌክትሪክን፣ እና ሌሎችንም መሠረተ ልማቶች ለኢኮኖሚው ማሳለጫ አድርጎ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በበጀት ዓመቱ ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት ባለቤት በመስጠት፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ተከታትሎ በመፍታት፣ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ መምራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

በዚህም ግልጽ እና አንድ ዓላማ በመያዝ በበጀት ዓመቱ ፕሮጀክቶች ከወረቀት ወደ መሬት፣ ወደ ማጠናቀቅ እና ወደ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚሸጋገሩበት ዓመት መኾን አለበት ብለዋል። ይህም ከሁሉም የመሠረተ ልማትን ከሚመሩ ተቋማት የሚጠበቅ ስለመኾኑም አሳስበዋል።

#አሚኮ #መሠረተ_ልማት #አማራክልል #ኢትዮጵያ

#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ጠንካራ የሀገር ግንባታ እና የትምህርት መሠረት የሚጣለው በቀዳማይ የልጅነት ዕድሜ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)