“ጠንካራ የሀገር ግንባታ እና የትምህርት መሠረት የሚጣለው በቀዳማይ የልጅነት ዕድሜ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

3

 

የአማራ ክልል የቀዳማይ ልጅነት ልማት የመረጃ መሠብሠቢያ ትውውቅ እና የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) “ጠንካራ የሀገር ግንባታ እና የትምህርት መሠረት የሚጣለው ልጆች ካደጉ በኋላ ሳይኾን በቀዳማይ ልጅነት ዕድሜያቸው ላይ ነው” ብለዋል። በመኾኑም ለሕጻናት በቂ ፍቅር፣ እንክብካቤ፣ ትምህርት፣ የቋንቋ እድገት እና የመጫወት መብትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ይህም ነገን የሚረከቡ፤ በራሳቸው የሚተማመኑ፤ ተወዳዳሪ እና ችግር ፈቺ ዜጎችን ለማፍራት ወሳኝ እንደኾነ ነው የገለጹት።

ዓላማውን ከግብ ለማድረስም እስካሁን ባለው ሂደት የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽነት ማሳደግ፤ የመምህራንን አቅም በሥልጠና መገንባት፤ የእናት እና ሕጻናትን ጤና ማሻሻል፤ የሕጻናት ማቆያ እና እንክብካቤ ማዕከላትን የማስፋፋት ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ ያሉትን ክፍተቶች በጥልቀት በመለየት የአምስት ዓመት የልጅነት ልማት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የዚህንም ዕቅድ አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተል እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሥርዓት (ዳሽቦርድ) ሥራ ላይ ውሏል ነው ያሉት።

ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ ተጀምሮ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በድሬዳዋ እየተተገበረ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ መሠረት ዘላለም (ዶ.ር) ናቸው። በተለይም የአማራ ክልል የቴክኒክ ቡድን በማደራጀት በአጭር ጊዜ ውስጥ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ዳሽቦርድ ማልማቱን አድንቀዋል።

የሕጻናት 80 በመቶው የአዕምሮ እድገት የሚከናወነው በመጀመሪያዎቹ ከ3 እስከ 6 ዓመታት ባለው ወሳኝ ጊዜ ውስጥ ነው ብለዋል። በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚደረግ የ1 ዶላር ኢንቨስትመንት እስከ 16 ዶላር የሚደርስ ሀገራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ማግኘት እንደሚቻልም ገልጸዋል። ለዚህም ሲባል በ2017 ዓ.ም በፓርላማ በጸደቀው አዋጅ መሠረት ሕጻናት ቢያንስ ለ2 ዓመታት በቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመቆየት ግዴታ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ራዕዩን በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል። ወላጆች ለሕጻናት ምላሽ ሰጪ እንክብካቤ፣ ፍቅር እና ትኩረት በመስጠት ትልቁን ድርሻ ሲወጡ፤ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ደግሞ በቤት ለቤት ጉብኝት ለወላጆች ግንዛቤ በመፍጠር ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል። በጨዋታ ላይ የተመሠረተ ትምህርት፣ የመጫወቻ ስፍራዎች እና የቀን እንክብካቤ ማዕከላት በስፋት መገንባት ለልጆቹ ሁለንተናዊ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አንስተዋል።

በ2019 በጀት ዓመት በሌሎች ክልሎችም ለማስፋት እንደሚሠራ ነው የጠቆሙት።

#ባሕር_ዳር #መስከረም_07_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🛺 “የዕለት ጉርሱን ሸጦ ለከተማው ክብር የገዛው የደሴው ብርቱ ወጣት!