ለሰላማዊ አማራጭ እና ለዘላቂ ልማት ቅድሚያ ተሰጥቷል።

5
የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ለሰላማዊ አማራጮች ቅድሚያ በመስጠት በዞኑ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።
የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው የሰላም እጦት በኅብረተሰቡ ላይ አስከፊ ችግር ጥሎ ማለፉን አስታውሰዋል። ባለፈው አንድ ዓመት ግን የከተማዋ ሰላም መሻሻሉን ገልጸዋል።
በዚህም የንግድ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ መነቃቃት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል። ለአዎንታዊ ለውጡ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ያደረገው ቅንጅት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ተናግረዋል።
የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አዱኛ መስፍን በአሁኑ ወቅት በፌዴራል፣ በክልል እና በከተማ አሥተዳደሩ በጀት የሚገነቡ የልማት ሥራዎች በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወኑ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
ለውጡ ዘላቂ እንዲኾን የሕዝብ እና የጸጥታ መዋቅሩ ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ በደጋማ የገጠር አካባቢዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የአካባቢው የጸጥታ ኀይል በመቀናጀት ባካሄዱት የሕግ ማስከበር ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በዞኑ ያለው አሁናዊ የሰላም አየር እና የልማት እንቅስቃሴ የሚሰራጩ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን የሚያከሽፍ መኾኑን ጠቁመዋል። አሁንም ለሰላማዊ አማራጮች ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የተከዜ ፖለቲካ” መጽሐፍ በስሜት ሳይኾን በስሌት የተጻፈ ብርቱ ሰነድ ነው።
Next articleሌተናል ጄኔራል ጥጋቡ ይልማ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኾነው ተሾሙ።