
የጦርነት እና የግጭት ዘላቂ መፍቻ መንገድ ውይይት እና ድርድር ነው። የሰው ልጅ በታሪኩ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ሲገጥሙት አስተማማኝ መፍቻ መንገዱ ውይይት እና ምክክር ነው።
በአማራ ክልል ይንቀሳቀሱ ከነበሩት የታጠቁ ኃይሎች መካከል የኮሎኔል ፈንታው መሀባው እና የካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ውሳኔ ይህንን እውነት በተግባር ያረጋገጠ፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን አስበልጦ የመረጠ ታሪካዊ እርምጃ ነው።
ኮሎኔል ፈንታው መሀባው እና ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ የሕዝባቸውን ጥያቄ እና ፍላጎት ለማስከበር በሚል የትጥቅ ትግልን መርጠው በጫካ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወሳል። በዚህ ሂደትም የገጠመው የሰው ሕይወት መጥፋት፤ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል፤ የንብረት ውድመት እና የሕዝቡ እንግልት ከባድ ገጽታዎች ነበሩት።
ትግሉ የመጣበትን ዋጋ ያስተዋሉት እነዚህ ወገኖች የኃይል አማራጭ ለሕዝቡ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ከማምጣት ይልቅ ቁስሉን የሚያባብስ መኾኑን ተገንዝበዋል። ታዲያ የትጥቅ ትግል የሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፍ ውጭ ትርጉም እንደሌለው በመረዳት ችግሮችን በውይይት እና በንግግር ለመፍታት የሰላምን አማራጭን ተቀብለዋል። ይህ ውሳኔ የሕዝብን ህመም ያደመጠ፤ አርቆ አሳቢነትን የተጎናጸፈ እና ለሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ቅድሚያ የሰጠ ታሪካዊ እርምጃ ነበር።
የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ከጫካ መውጣታቸው የትግል ዓላማቸውን የመተው ሳይኾን የሕዝብ ጥያቄዎችን በንግግር እና በምክክር ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል የሠለጠነ አካሄድ ነው። በአሁኑ ወቅት ሁለቱም በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መድረክ ላይ በንቃት እና በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምክክሩ የሕዝብን ጥያቄዎች በንግግር እና በምክክር በመፍታት ሀገርን የምናስቀጥልበት እና የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የምንቆርጥበት መድረክ ነው ብለዋል።
ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባው በበኩላቸው “የጫካ ትግል አያዋጣም እንጅ እኛም ነበርንበት ብለዋል። የሕዝብን ጥያቄ በኃይል ለማስመለስ መሞከር ለሀገርም፣ ለሕዝብም የማይበጅ እና መከራን ከመጨመር ባለፈ ምንም ጥቅም የሌለው መንገድ እንደኾነ ገልጸዋል። እነዚህ ወገኖች ቀደም ሲል በኃይል አማራጭ ለማስመለስ ይነሱ የነበሩ የማንነት፣ የወሰን፣ የፖለቲካ እና የመዋቅር ጥያቄዎችን በምክክር መድረኩ ላይ በግልጽ እና በሥነ-ሥርዓት በማቅረብ እና ጥያቄዎች በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ መልስ እንዲያገኙ እያቀረቡ መኾኑንም በተለያዩ ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ምክክሩ በሙሉ ነጻነት እና በጥሩ መግባባት እየተካሄደ መኾኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ በመድረኩ ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም የሚበጅ የጋራ ውሳኔ እንደሚደረስም ተስፋቸውን አንስተዋል።
የመንግሥት ጽኑ እምነት እና አቅጣጫ ማንኛውም ጥያቄ በሠለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ማድረግ ነው፤ በመኾኑም ታጥቀው ጫካ የገቡ አካላት የትጥቅ ትግል እንደማያዋጣ ተረድተው ጥያቄዎቻቸውን በምክክር እና በንግግር ብቻ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
