የባሩድ ጭስ ሳይኾን የብዕር ማዕዛን ለተማሪዎች መፍቀድ ግድ ይላል!

9
የተወሰኑ ሰዎችን የሥልጣን ጥም ለማርካት፤ የራስ ፍላጎትን ለማስከበር፤ የሕዝብን ጥያቄ በኃይል ለማስመለስ፤ በፍላጎት አለመጣጣም እና በበርካታ ምክንያቶች ግጭት ይፈጠራል።
ግጭት የንጹሐንን ሕይወት ይነጥቃል፤ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ያደርሳል፤ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲስተጓጎል፤ ረሃብ እና ድርቅ እንዲከሰት ያደርጋል። በተለይም የትውልድ ክፍተት በመፍጠር የተማረ የሰው ኃይል እንዲጠፋም መነሻ ይኾናል።
ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፤ እንዲወድሙ፣ ሕጻናት ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለጾታዊ ጥቃት እንዲጋለጡ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲፈጸምባቸውም ዕድል የሚሰጥ ነው።
በአማራ ክልል ከባርዱ ጭስ ይልቅ የብዕር ቀለምን የአሸናፊነት ዋጋ ያልተረዱ፤ የሰላምን በርከት በልባቸው ያላሠፈሩ፣ የሰላምን ቀጤማ ያልጨበጡ እጆች ሕጻት ከዕውቀት ድምጽ ይልቅ የጥይትን ድምጽ እንዲሰሙ አድርገዋቸዋል።
በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች ለበርካታ ጊዜ ጥቁር ሰሌዳዎች የጠመኔን ቀልም ናፍቀዋል፤ ወንበሮች የተማሪዎችን ደብተር ማስደገፍ ተመኝተዋል፤ ክፍሎች የሕጻናትን ድምጽ፣ ጨዋታ፣ ልብ የሚያሞቀውን የእውነት ፈገግታ ናፍቀዋል።
በክልሉ የጸጥታ ችግር ምክንያት 3 ሺህ 449 ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመለክታል። ያ ጥቁር ሰሌዳ የናፈቃቸው፣ በጠመኔ የሚከተበው የወደፊት ራዕያቸው በዓይናቸው የሚመላለስባቸው፤ ደብተር እና ብዕራቸውን በልጅ እጃቸው ማጣመር ያጓጓቸው፤ ከእኩዮቻቸው የሚቦርቁበት፤ አብሮነትን የሚማሩበት፤ ሰብዓዊነትን የሚቀስሙበት ትምህርት ቤታቸው የናፈቃቸው ከ3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በ2018 የትምህርት ዘመን ከትምርት ገበታ ሳይገኙ ቀርተዋል። ተማሪ ናቸውና ነገን በተስፋ እየጠበቁ ነው።
በ2019 የትምህርት ዘመን ደግሞ በትምህርት ገበታቸው ለመገኘት ልባቸው ተስፋን ሰንቋል። በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ የሰላምን ጮራ ይፈልጋሉ።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2019 የትምህርት ዘመን ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ እና ለማስተማር እየሠራ ይገኛል።
የልጆች ተስፋ እንደ ጤዛ እንዳይተን፤ ነጋቸው ዛሬ ላይ እንዳይሞት፤ ንጹሕ ፈገግታቸው እንዳይከስም፤ የእውቀታቸው በር እንዳይዘጋ ሰላምን ማጽናት የሁሉም ሰው ተግባር ሊኾን ይገባል።
የተማሪዎች የነገ ሕይወት በአንድ የጥይት ድምጽ ይጨልማልና ከባሩድ የጭስ ሽታ ይልቅ የብዕር ቀለምን ማዕዛ በትምህርት ቤት ተገኝተው እንዲምጉ መፍቀድ ግድ ይላል።
በያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article
Next article“የጫካው መንገድ አያዋጣም እንጅ እኛም ነበርንበት” የቀድሞ ታጣቂዎች