
የክረምቱን ማብቃት እና የአዲስ ዓመት መቃረብን የሚያበስሩ የእንግጫ ነቀላ እና ከስይ አጨዳ ባሕላዊ እሴቶች እንዳይበረዙ ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ለአሚኮ ገልጿል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ብርቄ ይዘንጋው እንደገለጹት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በልጃገረዶች እና ወጣቶች የሚከናወኑት እነዚህ ባሕላዊ ክዋኔዎች የማኅበረሰቡን አብሮነት እና መስተጋብር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው።
በዓሉ ወጣቶች እንግጫ በመንቀል፣ በመጎንጎን እና አደይ አበባ በመያዝ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን የሚያቀርቡበት በዓል ነው። በተለይም በሸበል በረንታ፣ በእነማይ እና በእናርጅ እናውጋ ወረዳዎች በስፋት በሚከበረው የከስይ አጨዳ ሥነ ሥርዓት፣ ወጣቶች መዓዛ ያለው የከስይ ዕጽዋትን በመቁረጥ እና በውብ ዜማ ታጅበው የአዲስ ዓመት ብስራትን እንደሚያበስሩ መምሪያ ኀላፊዋ አብራርተዋል።
እነዚህ የቆዩ ትውፊቶች በመጤ ባሕሎች እንዳይበረዙ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ብርቄ የዘንድሮው በዓል “ባሕላችን ድልድያችን፤ አንድነታችን መሻገሪያችን” በሚል መሪ መልዕክት በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች እና 8 የከተማ አሥተዳደሮች በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
