
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በደብረ ብርሃን ከተማ ጣይቱ ክፍለ ከተማ በሚገኘው አዲስ ከተማ የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ሊገነባ መኾኑን ገልጿል።
በሚኒስቴሩ መሪዎች እና ሠራተኞች በተመራው በዚህ መርሐ ግብር ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። የቦታ ርክክብ እና የችግኝ ተከላም ተከናውኗል።
የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ነጋሽ ተክሉ የነበረው የመማሪያ ቦታ ጠባብ በመኾኑ አዲሱ ግንባታ ለተማሪዎች እና መምህራን ዘላቂ እፎይታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ልዑል ስዩም እና የሴቶች እና ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳይ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኤልሳቤት ገብረ ሥላሴ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በለጋ ዕድሜ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት እና የሰው ሀብት ልማትን ለማጠናከር ያለመ ነው።
አዲሱ ትምህርት ቤት በቁሳቁስ የተሟላ እንደሚኾን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከተማሪዎች የቴክኖሎጂ አቅም ማዳበር ጋር አቀናጅቶ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሽት ድጋፉ ለትውልድ ግንባታ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ መኾኑን ጠቁመዋል። ማኅበረሰቡ ትምህርት ቤቱን እና የተተከሉ ችግኞችን በባለቤትነት እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
#Ameco #DebreBerhan #Ethiopia #Education🇪🇹
#ደብረ_ብርሃን #ነሐሴ_09_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
