በሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል።

6

 

በሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታውቋል።

የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሚ አብዱልዋሲ የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሃብት አልምቶ በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው ብለዋል።

ቱሪዝም ከዋና የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አንዱ ኾኖ መወሰዱ እና ትኩረት መሰጠቱ ዘላቂነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ከማልማት ባሻገር ነባር ቅርሶችን በመጠገን እና በመንከባከብ ረገድ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ እድሳትን ጨምሮ ነባር እና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሥራዎች እና መሰል ተግባራት የክልሉ ቱሪዝም በፍጥነት እንዲነቃቃ እያደረገ መኾኑንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት የሀገር ውስጥም ኾነ የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 14 ሺህ 700 የውጭ ሀገራት እና 180 ሺህ 754 የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የመስህብ ሃብቶችን ጎብኝተዋል ብለዋል።

በክልሉ የቱሪስት መስህብ ሃብቶችን የማስተዋወቅ፣ መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት እና መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ202 ሺህ 589 በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ 16 ሺህ 500 በላይ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የክልሉን የመስህብ ሃብቶች እንዲጎበኙ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።

#አሚኮ #ሐረሪ_ቱሪዝም #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_09_2018ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የካፍ መስፈርቶችን በማሟላት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲያካሂድ ተፈቀደለት።
Next articleየኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በደብረ ብርሃን ከተማ ደረጃውን የጠበቀ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው።