የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የካፍ መስፈርቶችን በማሟላት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲያካሂድ ተፈቀደለት።

7

 

የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስፈርቶችን በማሟላት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲያካሂድ ተፈቅዶለታል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ( ካፍ) የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም መስፈርቶችን ባለማሟላቱ ዓለምአቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያደርግ አግዶት ቆይቷል።

በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሌሎች ሀገራት እንዲጫወት ተገድዶ ቆይቷል። ካፍ የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም የዓለም አቀፍ ስታዲዬም ማሟላት የሚገባውን መስፈርት እንዲያሟላ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።

ባለፉት ዓመታት ስታዲዬሙ የካፍ መስፈርቶችን ባሟላ መልኩ ግንባታ ሲካሄድለት ቆይቷል። አሁን ላይ መስፈርቶችን በማሟላት ማረጋገጫ ተሰጥቶታል።

የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ ለአሚኮ እንደገለጹት ለበርካታ ዓመታት የዓለም አቀፍ ውድድሮች እገዳ ተጥሎበት የቆየው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተደረገለት ሰፊና ዘመናዊ የሁለተኛ ምዕራፍ የማሻሻያ እና የግንባታ ሥራ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) መስፈርቶችን በማሟላት ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጁ መኾኑ ተረጋግጧል ብለዋል።

ይህ ትልቅ የስፖርት ስኬት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) እና ክለቦች አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ውድድሮችን በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት እንዲያደርጉ ያስችላል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ወደፊት አበይት የአህጉር አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የምታደርገውን ጉዞ ያፋጥነዋል ብለዋል። ይህ ስኬት በመገኘቱ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዲያደርግ ፈቃድ ማግኘቱ የአማራ ክልል እና የመላው ኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በታሪካዊ ፣ በተፈጥሯዊ እና በባሕላዊ የቱሪዝም ሃብቶች ለታደለው የአማራ ክልል ተጨማሪ ሃብት ነው።

Previous articleየሻደይ በዓልን በብሔረሰብ ደረጃ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
Next articleበሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል።