
ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ መሠረት ያለው የልጃገረዶች እና የሴቶች በዓል የኾነው የሻደይ በዓል ከነሐሴ 16/2018 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም በብሔረሰብ ደረጃ በድምቀት እንደሚከበር የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ገልጿል።
በበዓሉ ዝግጅት ላይ የሚሳተፉት የሰቆጣ ከተማ የሻደይ ተጫዋቾች ቅድስት ነጋሽ እና ዓለም አበራ ሻደይ የልጃገረዶች መድመቂያ ብቻ ሳይኾን እህታማችነትን የሚያጠናክር በዓል መኾኑን ጠቅሰዋል። የአካባቢያቸውን ባሕል፣ አጊያጊያጥ እና ዜማ ለማቅረብ እየተዘጋጁ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ከልጅነታቸው ጀምረው ሲጫወቱ ያደጉት የ70 ዓመቷ እናት ወይዘሮ አለሙሽ ፈረደ እናቶች ያሳለፉትን አጨዋወት፣ ዜማ እና ሥነ ቃል ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ካሳ ከበደ ከተማዋን የሚወክሉ ታዳጊዎችን፣ ወጣቶችን እና እናቶችን መልምለው እያዘጋጁ መኾናቸውን አስታውቀዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ይርጋ ማርየ በዓሉ በብሔረሰብ ደረጃ ቢከበርም ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ በሁሉም የብሔረሰቡ አካባቢዎች በታላቅ ድምቀት እንደሚከበርም ጠቁመዋል።
#Ameco #ሻደይ #ድንቅባሕል🇪🇹
#ሰቆጣ #ነሐሴ_09_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
