
ከምሥረታው ጀምሮ ከአንድነት ይልቅ የልዩነት ፍሬን የዘራ፤ አብሮ ከመኖር ይልቅ መለያየትን የመረጠ፤ ከሰላም ይልቅ ግጭት እና ጦርነትን ማደሪያው ያደረገ፤ ከልማት ይልቅ ጥፋት ሱስ የኾነበት ቡድን ነው ሕገ ወጡ ሕወሃት።
ከትግል መስመር እስከ ርዕዮተ ዓለም፤ ከንድፈ ሐሳብ እስከ ተግባራዊ ፖለቲካ ሥርዓቱ ድረስ ከሀገር እና ሕዝብ ፍጹም የተቃረነ ነው።
የፖለቲካ ፍላጎቱን ለማርካት የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የሕዝብን ጥቅም እና ደኅንነት አሳልፎ ከመስጠት ወደ ኋላ የማይል መኾኑን ደጋግሞ አሳይቷል። በሀገር እና ሕዝብ ላይ የፈጸመው በደል ጸሐይ የሞቀው ሀገር ያወቀው ነው።
ይህ ሕገ ወጥ ቡድን ከተመሠረተበት 1960ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ የተከተለው ጠባብ የብሔረተኝነት እሳቤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ አንድነት እና እድገት አሁንም ድረስ መዥገር ኾኖ ይገኛል። ከሥልጣን ቢወገድም በመላ ሀገሪቱ የዘራው መርዝ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያን እያቆሰለ ይገኛል።
የአንድነት፣ የአብሮ መኖር እና መሰል መልካም ኢትዮጵያዊ እሴቶች ጸር መኾኑን አሳይቷል። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ዛሬም ድረስ ለሚከሰቱ ግጭቶች እና አለመግባባቶች መነሻው ይሄው ሕገ ወጥ ቡድን ነው።
ከተከለው ብሔር ተኮር የፖለቲካ ሥርዓት ባለፈ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የተከተለው “እኔ ከሞትኩ …” ዓይነት አቋሙ ሀገሪቱን ለከፋ ጦርነት እና ውድመት ዳርጓታል።
የዚህ ቡድን ክፋቱ የኢትዮጵያን እድገት አለመፈለጉ ብቻ አይደለም። ሀገሪቱ ባላት ጸጋ ልከ እንዳታድግ ለማድረግ ያላት ጸጋ እንዳይታወቅ ብሎም እንደ እርግማን እንዲቆጠር መሥራቱም ጭምር ነው።
ይህ የሀገር ጠላት የኾነ ሕገ ወጥ ቡድን የሕዝብ ቅቡልነት ኖሮት አያውቅም። በዚህ የተነሳ ሁልጊዜም ቢኾን ብቻውን መቆም አይችልም። ታዲያ ሕልውናውን ለማስቀጠል ተመሳሳይ ግብር ካላቸው የሀገር ውስጥ ሕገ ወጥ ታጣቂዎች እና ከሀገሪቱ የውጭ ጠላቶች ጋር በተደጋጋሚ አጋርነት ሲፈጥር ታይቷል።
በ1960ዎቹ በተንቤን በረሃ የትጥቅ ትግል ታሪኩ እንደ ግብፅ እና ሻዕቢያ ካሉ የሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ደመኞች እና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ትብብር መሥርቶ እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች በተደጋጋሚ ያረጋገጡት ገዳይ ነው።
ከታሪክ ስህተቱ የማይማር ቡድን መኾኑ ደግሞ የቡድኑን አስከፊነት ከፍ ያደርገዋል። በሕዝብ በቃህ ተብሎ ከሥልጣን ተወግዶም ከአውዳሚ አካሄዱ ዛሬም ድረስ አልተገታም። ከሕገ ወጥ ታጣቂዎች፣ እንደ ግብፅ እና ሻዕቢያ ካሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተለመደ ያልተቀደሰ ሽርክናውን በመመለስ ኢትዮጵያን ከሁለንተናዊ ልማት እና እድገቷ ለማደናቀፍ ላይ ታች እያለ ይገኛል።
ሕገ ወጡ ሕወሃት በሥልጣን ዘመኑ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አንዳች አጋርነት ሲፈጥር አልታየም። ሁለንተናዊ አጋርነት የሚመሠርተው ሀገርን በጋራ ለማልማት ሳይኾን በጦርነት የዜጎችን ሕይወት ለመቅጠፍ እና የሀገርን ሐብት ለማውደም ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ ሕገ ወጡ ሕወሃት የደርግ መንግሥትን አሸንፎ ሥልጣን የያዘው በራሱ ሳይኾን በሌሎች ድጋፍ እና እገዛ መኾኑን ተናግረዋል። አሁንም ተደግፎ የኾነ ነገር ማድረግ የሚችል ይመስለዋል በማለት ቡድኑ በውጭ ጠላቶቻችን ተገዝቶ ኢትዮጵያን በመረበሽ፣ ሰላም በማሳጣት መቀጠል ፍላጎቱ መኾኑንም አስረድተዋል።
አሁን ግን ከምኞት የዘለለ የሚያደርገው ነገር የለም። ተቸንካሪው ቡድን ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶች ጋር ቢፍጨረጨርም ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይቻልም።
#Ameco #NoMoreWar #ሰላም #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_09_2018ዓ_ም
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
