
አቶ ምትኩ ይትባረክ በባሕር ዳር ከተማ የግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። የእግር አካል ጉዳተኛ እና ጡረተኛ የኾኑት እኒህ አባት ከልጆቻቸው መካከል ሦሥቱ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ። አንደኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ሲኾን ቀሪዎቹ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው።
እኝህን አባት የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ “አንድ ደርዘን ለአንድ ተማሪ” በሚል ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ላላቸው ተማሪዎች ባደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የዕድሉ ተጠቃሚ ኾነው አግኝተናቸዋል።
ለልጅ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ያለውን ፈተና ሲናገሩ ልጆቸ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የትምህርት ቁሳቁስ ያሳስባቸዋል። ወላጆች ደግሞ የልጆቻችንን ፍላጎት ለማሟላት እጅጉን እየተቸገርን እንገኛለን ነው ያሉት።
አካል ጉዳተኛ እና ጡረተኛ በመኾናቸው ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት እንደሚቸገሩም ተናግረዋል። ነገር ግን ልጆቼን ለቁም ነገር ማብቃት ስላለብኝ ወገቤን አስሬ እያስተማርኩ ነው ይላሉ።
አቶ ይትባረክ ለአካል ጉዳተኛ እና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ላላቸው ወላጆች ዩኒፎርም፣ ደብተር እና እስክርቢቶ አሟልቶ ልጅን ማስተማር ከባድ ፈተና በኾነበት በዚህ ወቅት በክረምት በጎ ፈቃድ የሚደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እጅግ አስደሳች ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል መንገድ ትራንፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ የትራንስፖርት አገልግሎት ስምሪት ዳይሬክተር ጌታቸው መርሻ በዚህ ክረምት በመናኾሪያዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን ለማከናወን ከ 12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን ጠቁመዋል። ከዚህ ውስጥ በባሕርዳር ከተማ ጣና በር እና ጎጃም በር መናኾሪያዎች ከ220 ሺህ ብር በላይ በኾነ ወጭ ለ200 ተማሪዎች የደብተር እና እስክርቢቶ ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል መንገድ ትራንፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዘውዱ ማለደ ቢሮው ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን በውጤታማነት እየፈጸመ መኾኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙትን መናኾሪያዎች ከኋላ ቀር አሠራር ወጥተው የተሳለጠ ትራንስፖርት ከመስጠት ባሻገር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት እየተሳተፉ መኾናቸውን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በአሸከርካሪ ማሠልጠኛ ተቋማት እና በሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት የበጎ አድራጎት ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
በመንገድ ትራንፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፍ በዚህ ዓመትም ከ90 ቀናት ዕቅዶች መካከል የኾነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰው ተኮር ተግባር በውጤታማነት እየተፈጸመ መኾኑንም አረጋግጠዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የጣና በር እና ጎጃም በር መናኾሪያዎች በሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት እና በመናኾሪያ ሠራተኞች አስተባባሪነት የተደረገው ድጋፍ የሚበረታታ እና በኹሉም ዞኖች እየተተገበረ ያለ ነው ብለዋል።
#Ameco #VolunteeringStudents #Ethiopia 🤝 🇪🇹
#ባሕር ዳር #ነሐሴ_09_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
