በባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

5

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በባሕር ዳር ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የወጣቶች ቀን ሲከበር ዝም ብሎ ከማክበር ባለፈ ሀገራዊ ኀላፊነትን በመውሰድ እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ ሊኾን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ካለው የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ወጣቶችን ታሳቢ ያላደረገ ሀገራዊ ጉዞ ውጤታማ ሊኾን እንደማይችልም ተናግረዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተለዩት 17 ዋና ዋና ተግባራት መካከልም ወጣቶች ፊት አውራሪ በመኾን ለአረጋውያን፣ ለሕጻናት፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የሚያደርጉበት ሥራ እንደኾነ ገልጸው በዚህም ወጣቶች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል።

የበጎ ፈቃድ ሥራው እስከ መጭው መስከረም መጨረሻ አካባቢ የሚቀጥል እና በቀጣይም በበጋ እንደሚተካ አመላክተዋል።

መምሪያውም ከክልል ቢሮዎች እና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመኾን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እየሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።

የወጣቶች ቀን በዓል ተሳታፊ ወጣቶች ደግሞ የቀኑ መከበር ከበዓልነቱ ባለፈ ለወጣቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ነግረውናል። የወጣቶች ሀሳብ እንዲሰማ፣ የተለያዩ ክህሎቶቻቸው እንዲታዩ እና አቅሞቻቸውን ተጠቅመው በጋራ ሠርተው ተጠቃሚ እንዲኾኑ ያግዛልም ብለዋል።

በቀጣይም ለወጣቶች ተጠቃሚነት ሲባል በየዓመቱ የወጣቶችን ቀን ከማክበር ያለፈ ሥራ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።

በክረምት በጎ ፈቃድ እና በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፉ መኾናቸውን የገለጹት ወጣቶች ያላቸውን ንቁ ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

#Ameco #InternationalYouthDay #BahirDar_Ethiopia🇪🇹

#ባሕር ዳር #ነሐሴ_09_2018_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleወልቃይት ጠገዴ የኢትዮጵያ ሳንባ ናት ፤ ተከዜ ደግሞ የደኅንነት እና የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው!
Next articleየአማራ ክልል መንገድ ትራንፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ 13 ሚሊዮን በሚጠጋ በጀት የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።