
በቹቹ አለባቸው (ዶ.ር) የተጻፈው “የተከዜ ፖለቲካ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ በጎንደር ከተማ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በምረቃው ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንደገለጹት መጽሐፉ የተከዜን ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ በጥልቀት የሚዳስስ እና የተፈጥሮ ሀብትን በበጎ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል ያለውን አስተዋጽኦ የሚተነትን ነው።
አቶ ቻላቸው አክለውም ተከዜ የቦታ፣ የደኅንነት፣ የትውልድ እና የኢኮኖሚ ጥያቄ መኾኑን ጠቅሰው ብሔራዊ ደኅንነት በጦር መደራጀት ብቻ ሳይኾን በኢኮኖሚ፣ በተማረ ሕዝብ እና በማኅበራዊ ትስስር የሚረጋገጥ መኾኑን መጽሐፉ ማብራራቱን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አሥፈሬ በበኩላቸው፣ ጸሐፊው የሕዝብ የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች ላይ በጽናት ሲታገሉ የቆዩ መኾናቸውን አንስተዋል።
መጽሐፉ በተከዜ ተፋሰስ እና በወልቃይት ጉዳይ ላይ የሚያተኩር በመኾኑ ለፖለቲከኞች እና ለፖሊሲ አውጭዎች ጠቃሚ ግብዓት እንደሚኾንም አስረድተዋል።
የመጽሐፉ ደራሲ ዶክተር ቹቹ አለባቸው መጽሐፉን ያዘጋጁበትን ዓላማ ሲያስረዱ መረጃዎች ለትውልዱ በግልጽ እንዲደርሱ እና ብዥታዎች እንዲወገዱ በማሰብ እንደኾነ ገልጸዋል።
ወልቃይት ጠገዴን “የኢትዮጵያ ሳንባ እና ሆርሙዝ” ሲሉ የገለጹት ደራሲው ተከዜ የውኃ ሀብት ብቻ ሳይኾን የደኅንነት እና የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመኾኑ “ወልቃይትን መጠበቅ ኢትዮጵያን መጠበቅ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። በቹቹ አለባቸው (ዶ.ር) የተጻፈው “የተከዜ ፖለቲካ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ በባሕር ዳርም መመረቁ ይታወሳል።
#Ameco #TekezePolitics #Wolkait #EthiopianPolitics🇪🇹
#ጎንደር #ነሐሴ_09_2018_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ፦አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
