በጋራ ቁርጠኝነት ትምህርት ቤቶችን መክፈት፣ መልሶ መገንባት እና ተስፋን መዝራት ያስፈልጋል።

10

 

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አሥተባባሪነት 23ኛው የአማራ ትምህርት ክልላዊ ልማት ትብብር ፎረም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ አጋር አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንት አደመ ባለፉት ዓመታት በትምህርቱ ሥርዓት ላይ የተገኙ ስኬቶች እና ጉድለቶችን በመመልከት ውጤታማነትን ማረጋገጥ የውይይቱ ዓላማ መኾኑን ተናግረዋል። መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች የትምህርት ዘርፉን እንዲደግፉ ለማስቻል ያለመ መኾኑንም አንስተዋል።

ውይይቱ ለትምህርት ብቻ ሳይኾን የልጆችን እና የሀገርን የቀጣይ ድል የሚወስን ነው ብለዋል። በውይይቱ የትምህርት ችግሮችን ለመለየት፣ መነሻ መንስኤዎችን ለማወቅ እና መፍትሔዎችን በጋራ ለማስቀመጥ ያለመ ውይይትን ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት።

በ2019 የትምህርት ዘመን ሁሉም ለትምህርት ዕድሜያቸው የደረሱ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።

በጋራ መሥራት በመቻሉ በግጭት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት ተችሏል ነው ያሉት። በጋራ መሥራት ውጤታማ ማድረግ እንደሚችል ተመልክተናልም ብለዋል።

በ2018 የትምህርት ዘመን ከ3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ሳይመዘገቡ መቅረታቸውን አንስተዋል። በጸጥታ ችግር ምክንያት ከ1ሺህ 400 በላይ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ አለማካሄዳቸውንም ገልጸዋል። 3 ሺህ 449 ትምህርት ቤቶች በክልሉ ውስጥ ባለው ግጭት ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል።

ከትምህርት ገበታ ውጭ የሚኾኑ ተማሪዎች ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለያለዕድሜ ጋብቻ፣ ለጠለፋ እና ለተያዩ ጉዳቶች እየተጋለጡ ነውም ብለዋል።

በ2019 የትምህርት ዘመን ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ እና የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት። የትምህርት ቤቶችን፣ የመምህራንን እና የተማሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።

የትምህርት ዘርፉን መንግሥት ብቻ ውጤታማ ማድረግ አይችልም ያሉት ምክትል ኀላፊው የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ርብርብ እንዲያደርጉም አሳስበዋል። በጋራ ቁርጠኝነት ትምህርት ቤቶችን መክፈት፣ መልሶ መገንባት እና ተስፋን መዝራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የትምህርት ቢሮን ዕቅድ መነሻ በማድረግ አጋር እና ባለድርሻ አካላት የትምህርት ዘርፉን ሊደግፉ እንደሚገባም አሳስበዋል። ትምህርት ቤቶች የግጭት መዳረሻ እንዳይኾኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት።

#አሚኮ #ትምህርት #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_09_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበደብረታቦር ቀጣና የተሠማራው የምሥራቅ ዕዝ ኮር የፅንፈኞችን የጥፋት መሰናክሎች በማፅዳት ሰላም እያሰፈነ ነው።
Next article🏫 📚ኢዜአ በባሕር ዳር ከተማ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች ግንባታ አስጀመረ።