
በአደጋ፣ በምጥ እና በጽኑ ሕመም ምክንያት በሕይወት እና በሞት መካከል ለሚታገሉ ወገኖቻችን ከእኛ የሚጠበቀው ትልቁ ስጦታ “አንድ ጠብታ ደም” ነው።
በሕይወት ውስጥ ትልቁ ስጦታ ገንዘብ ወይም ቁሳቁስ ሳይኾን ለሌላው የሚሰጥ የሕይወት አድን ነው። የሰውን ሕይወት ለመታደግ የራስን ደም በፈቃደኝነት መስጠት ከሁሉም በላይ የላቀ የሰዋዊነት ማሳያ ነው።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪው ታደሰ አሰፋ ይህን የከበረ ሰዋዊ እሴት በተግባር በመተርጎም የብዙዎችን ሕይወት ከታደጉ ግለሰቦች አንዱ ናቸው።
አቶ ታደሰ በገንዳ ውኃ ከተማ ለረጅም ጊዜ በሚያደርጉት ደም የመለገስ በጎ ተግባራቸው በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ። ለእሳቸው ደም መስጠት ወቅታዊ ተግባር ሳይኾን ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያለምንም ማቋረጥ የተጓዙበት የሕይወት ዘመን መንገድ ነው።
“በደም እጦት ምክንያት አንዲት የሰው ሕይወት እንኳ በከንቱ እንድታልፍ አልፈልግም” ይላሉ። በእነዚህ ረጅም ዓመታት ውስጥ በለገሱት ደም ስንት ሕይወት እንደታደጉ ሲያስቡ የሚያገኙት ውስጣዊ እርካታ ወሰን እንደሌለው ገልጸዋል።
ለእሳቸው ትልቁ ሀብት እና ደስታ የወገንን ሕይወት መታደግ መቻላቸው ነው። ይህን በጎ ተግባር የዕለት ተዕለት ባሕል በማድረግ ወደፊትም ደም መለገሳቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
ይህን የሕይወት አድን በጎ ተግባርም የኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ ኅዋስ ባንክ አገልግሎት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሕል አድርጎ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ደም እና ኅብረ ኅዋስ ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ዶክተር መላሽ ገላው እንደገለጹት ከሐምሌ/2018 ዓ.ም እስከ መስከረም/2019 ዓ.ም በሚቆየው የሦሥት ወር የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ የደም ልገሳ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።
በዚህ የሦሥት ወር የዘመቻ ጊዜ ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ 150 ሺህ ዩኒት ደም ለመሠብሠብ ታቅዷል። 110 ሺህ ዩኒት ደም የሚኾነው በክልሎች 40 ሺህ ዩኒት ደም የሚኾነው ደግሞ በአዲስ አበባ የሚሠበሠብ ነው ብለዋል።
በሐምሌ/2018 ዓ.ም ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ 61 ሺህ ዩኒት ደም መሠብሠብ መቻሉን ገልጸዋል።
ወጣቶች፣ የግል እና የመንግሥት ተቋማት ኅብረተሰቡ ደም እንዲለግስ በመቀስቀስ እና በማስተባበር በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፉ መኾናቸውንም አብራርተዋል።
ይህ የክረምት ዘመቻ ሁሉንም የደም ዓይነቶች እና የሚፈለገውን መጠን ለማግኘት ትልቅ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል። ባለፉት ጊዜያት አልፎ አልፎ ያጋጥም የነበረው የደም እጥረት አሁን ላይ በሀገር ደረጃ እንደሌለም አረጋግጠዋል።
ደም መለገስ የሕይወት ስጦታ በመኾኑ ጊዜ፣ ወቅት እና ቦታ የሚገድበው መኾን የለበትም፤ በመኾኑም ኅብረተሰቡ ከወቅታዊ ዘመቻዎች ባሻገር በተለመደው እና በመደበኛው ጊዜ ሁሉ ደም የመለገስ ባሕሉን ሊያጠናክር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
