📌 ከአፈር ነዳጅ ለማዘጋጀት የተወጠነው ፈጠራ የት ደረሰ?

26

ከአስር ዓመታት በፊት በነዳጅ እና በሊቲየም ፈጠራ ሥራቸው የብዙዎችን ትኩረት ስበው የነበሩት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ መምህር እና ተመራማሪው አቡሃይ ውብሸት አሁን ፈጠራው ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

እርሳቸው እና ሌሎች ጓደኞቻቸው የጀመሩት ከአፈር ነዳጅ የመፍጠር የምርምር ፕሮጀክት ትንንሽ የላቦራቶሪ ሙከራዎችን (በሚሊ ሊትር ደረጃ የነበሩትን) አልፎ በሊትር ደረጃ (ከ30 እስከ 40 ሊትር) ማምረት የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱን ነግረውናል።

ለፈጠራው የባለቤትነት (የፓተንት) መብት ማግኘቱንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የጥራት ኤጀንሲ ምርቱ ለተሽከርካሪዎች መዋል እንደሚችል የጥራት ማረጋገጫ እንደሰጣቸውም አንስተዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት ነዳጁ ተመርቶ የተወሰኑ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሎ እንደነበረም አስታውሰዋል። በዚያው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እያገለገሉ ከሚገኙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ አንዷለም ጋር በመኾን ለቀረበው ለዚህ የምርምር ውጤት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እውቅና እና ሽልማት እንደተበረከተላቸውም ተናግረዋል።

ለዚሁ ምርት ግብዓት የሚኾነውን ዶቤ የተባለ የአፈር አይነት መኾኑን ጠቅሰዋል። ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ግን በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለጥሬ ዕቃት የሚያገለግለውን የዶቤ አፈር ናሙናዎችን በማጥናት ሥራው ሙሉ በሙሉ ወደ ፋብሪካ እና ሰፊ ምርት እንዳይሸጋገር የጸጥታ ሁኔታው አስቸጋሪ እንደኾነባቸው ነው የተናገሩት።

የፕሮጀክቱን አዋጭነት በሰፊው ለማጥናት ግብዓቱ በበቂ ሁኔታ የመገኘቱን አቅም ለማረጋገጥ የሚረዳ የፋይናንስ እጥረት እንደገጠማቸውም አንስተዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ እገዛዎችን እያደረገላቸው እንደኾነም ጠቅሰዋል። በዩኒቨርሲቲው በየጊዜው በሚደረጉ የአመራር ለውጦች ምክንያት በሚፈጠሩ አሠራሮች ግን እክሎች እየገጠሟቸው እንደነበር ነው የጠቀሱት።

ከአፈር ነዳጅ የመፍጠር ፕሮጀክቱ አሁንም አልተቋረጠም ያሉት መምህር እና ተመራማሪ አቡሃይ በላቦራቶሪ ደረጃ ሥራው ቀጥሏል ብለዋል። ከባዮነዳጁ በተጨማሪ ለኤሌክትሪክ መኪናዎች እና ለወደፊት ኢነርጂ ወሳኝ የኾነውን የሊቲየም ማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ትልቅ ውጤት ማምጣታቸውንም ጠቁመዋል።

በቀጣይ ለሙያው ቅርብ የኾኑ ባለሀብቶች፣ የመንግሥት አካላት እና በጎ አድራጊ ድርጅቶች አብረው በጥናት እና በፋይናንስ ቢደግፏቸው የጥሬ ዕቃ ክምችቱን አጥንተው ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ለመግባት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የጎንደር ዩኒቨርስቲው ተመራማሪ አቡሃይ ውብሸት በሰሜን ተራራ የሚገኝ ዶቤ የተሰኘ አፈርን ከውኃ ጋር በመቀላቀል እና በተለያየ ደረጃ የሙቀት መጠን በማሳለፍ የተጣራ ነዳጅ ማግኘታቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል መዘገቡ የሚታወስ ነው ።

#AMECO #የፈጠራ #ሳይንስና_ቴክኖሎጂ

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_08/2018/ዓ.ም

✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article​ “ሕይወት እንዳዳንኩ ሳስበው የማገኘው ውስጣዊ እርካታ ወሰን የለውም” ደም ለጋሽ
Next article“ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ እና አስተማማኝ መሠረት ለመጣል የተቀናጁ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነáˆ