“ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራ እና አስተማማኝ መሠረት ለመጣል የተቀናጁ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

6

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አረንጓዴ ዐሻራ – ተፈጥሮን ከመንከባከብ እስከ ሀገራዊ የምግብና ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የሚደርስ መኾኑን አንስተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ከመትከል ወይም አካባቢን ከማስዋብ የዘለለ፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠበቅ፣ የማልማትና የዘላቂ ልማታችንን መሠረት የማጠናከር ስትራቴጂያዊ ሀገራዊ እርምጃ መኾኑን በተግባር እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም አቅማችንን ከማጠናከሩም በላይ፣ የተፈጥሮ ስነ ምህዳራችንን በማስተካከል እና በማልማት ኢትዮጵያን አረንጓዴ ምድር እያደረጋት ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትም ኢትዮጵያ በራሷ አቅምና በዜጎቿ የጋራ ጥረት የተፈጥሮ ሀብቷን መጠበቅና ማልማት እንደምትችል ያረጋገጡ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ረገድ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሚኾኑ የወል ስኬቶች ናቸው።

የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይኾን፣ ለግብርና ምርታማነት፣ በምግብ ራስን ለመቻል እና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረት ነው። ለዚህም ነው አረንጓዴ ዐሻራን የምግብና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ለማጠናከር ዋነኛ ዘላቂ ሀገራዊ የልማት ትኩረታችን ያደረግነው ብለዋል።

ይህ ትውልድ የተፈጥሮ ሀብቱን በመጠበቅና በማልማት የዚህ ዘመን መሻቱን ከማሟላት ባለፈ፣ ለመጪው ትውልድ የበለጸገች እና የማትበገር ኢትዮጵያን የማስረከብ ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት።

ለነገዋ ኢትዮጵያ ጠንካራና አስተማማኝ መሰረት ለመጣል ለዚህ ደግሞ የጀመርናቸውን የተቀናጁ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

#አረንጓዴ_አሻራ_Green_Legacy

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_08_2018_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article📌 ከአፈር ነዳጅ ለማዘጋጀት የተወጠነው ፈጠራ የት ደረሰ?