
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን የ2019 የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የ2019 በጀት ዓመት የትምህርት ዘመንን ስኬታማ ለማድረግ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በየደረጃው ያሉ መምህራንን የማሠልጠን፤ የትምህርት ግብዓቶችን የማሟላት፤ የትምህርት ቁሳቁስ የማሰባሰብ፣ ትምህርት ቤቶችን ምቹ እና ሳቢ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር አማካኝነት በ1 ሺህ 205 ትምህርት ቤቶች ከ138 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መሥጠት መቻሉንም አንስተዋል።
በ2019 የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል ከቅድመ-አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ እና ለማስተማር መታቀዱንም አስታውቀዋል።
ምዝገባውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ካለፉት ዓመታት በተለየ መንገድ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል። በዚህም የ2019 የተማሪዎች ምዝገባ በልዩ ንቅናቄ ከነሐሴ 18 እስከ ጳጉሜ 5/2018 ዓ.ም ድረስ ለማከናወን በዕቅድ ተይዟል ነው ያሉት።
መስከረም 5/2019 ዓ.ም ደግሞ መደበኛ ትምህርት የሚጀመርበት ቀን ነው ብለዋል። በትምህርት ዘመኑ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ክፍት ኾነው የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲከናወን ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
ከነሐሴ 13 እስከ 15 በባሕር ዳር ከተማ ከልዩ ልዩ አካላት የትምህርት ቁሳቁስ የሚሰበሰብበት እና ርክክብ የሚደረግበት መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል ነው ያሉት።
ሦስት የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ትምህርት ለማስጀምር ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
የ2019 የትምህርት ዘመን ስኬታማ እንዲኾን የሃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ወጣቶች፣ ምሁራን እና የሚመለከታቸው አጋር አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
#Ameco #Education #አማራ_ክልል
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_08_2018ዓ_ም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
