
የባሕር ዳር ከተማ ምክር ቤት አባላት፣ የከተማዋ ነዋሪ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች እና ወጣቶች በከተማዋ የተሠሩ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ጎብኝዎች የራቫል ብረታ ብረት ፋብሪካን፣ በድባንቄ ተራራ ላይ የተሠራ የእርከን ሥራ፣ የአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም መልሶ ግንባታ፣ በከተማዋ የተሠሩ የኮሪደር ልማቶች፣ የተቀናጀ የዶሮ ማርቢያ (የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ፣ ማሳደጊያ፣ ምርት ማስቀመጫ እና መሸጫ) ሼዶች ግንባታ፣ የኮበል ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር የከብት ማድለብ፣ የእንጨት እና ብረታ ብረት መሥሪያዎችን ነው የጎበኙት።
የጉብኝቱ አስተባባሪ የባሕርዳር ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ጌትነት እውነቱ (ዶ.ር) የጉብኝቱ ዋና ዓላማ ኅብረተሰቡ የኮሪደር፣ የፓርኮች እና የፋብሪካዎች ልማትን አይቶ እና ተረድቶ ልማቱ የበለጠ እንዲጠናከር በሃሳብ፣ በገንዘብም ኾነ በጉልበቱ እገዛ እንዲያደርግ ለማስቻል መኾኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር ምክርቤቱ በዕቅድ ወቅት እነዚህን የልማት እንቅስቃሴዎች በመገምገም የ2019 ዕቅድ የሕዝቡን ተጠቃሚነት እና የወጣቶችን የሥራ ዕድል በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲቃኝ ለማስቻል ነው ብለዋል።
የተጀመሩት የኮሪደር ልማቶች፣ የከተማ ውበት ሥራዎች እና የኢንዱስትሪ መስፋፋቶች የከተማን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ እንደሚገኙም አንስተዋል።
የከተማዋ ልማት ዘላቂ ይኾን ዘንድም ማኅበረሰቡ የሚያደርጋቸውን እገዛዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። የጋራ ጥረት ለተሻለች ባሕር ዳር አስፈላጊ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ደግሞ ከከተማ ልማት አኳያ በጉብኝታቸው ብዙ ለውጥ መመልከታቸውን ገልጸዋል። በተለይ በኢንዱስትሪዎች እና በስታዲየሙ መልሶ ግንባታ ላይ የተሠሩ ሥራዎች የሚደነቁ መኾናቸውን ነው ያነሱት። ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያ የነበሩ ቦታዎች አሁን አምረው እና ተውበው በማየታቸው ደስተኛ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ሕዝቡም ይህንን ልማት በአቅሙ መደገፍ እንዳለበት እና እነርሱም የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
#Ameco #BahirDarDevelopment #TogetherForBahirDar
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_08_2018_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
