ወጣትነትን ለሀገር ሕልውና እና ለልማት ማዋል ይገባል።

7

“ብዝኀ የወጣቶች ዕውቀት ለጋራ ትልም” በሚል መሪ መልዕክት 23ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ላይ የሰላም ሚኒስቴር መሪዎች፣ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የወጣቶች ማኅበር ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የአማራ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ወጣት አንተነህ ገብረ ሚካኤል እንደገለጸው ዕለቱን ማሰብ ወጣቶች በሀገር ፖሊሲ ቀረፃ እና በሰላም ማስፈን ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ ነው።

ማኅበሩ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ መኾኑን ጠቅሷል። ወጣት አንተነህ ገብረ ሚካኤል ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ጥያቄዎች በውይይት እና በመነጋገር መፍታት እንዳለባቸው አሳስቧል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሙሉቀን ጌታሁን ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። ወጣትነትን ለሀገር ሕልውና እና ለልማት ማዋል እንደሚገባም ገልጸዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የብቃት እና የሰው ኀይል ዋና አሥተዳዳሪ ኮሪ አብደላ ወጣቶች በሥነምግባር የታነጸ የሰላም አምባሳደር መኾን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶችም ስለ ሰላም አስፈላጊነት ግንዛቤ በመፍጠር ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

#Ameco #InternationalYouthDay

#ጎንደር #ነሐሴ_08_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ማህደር አድማሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየጋራ ጥረት ለተሻለች ባሕርዳር!
Next articleዓባይን በስኬት አጠናቅቀናል፤ ወደ ቀይ ባሕር ተመልሰናል !