ዓባይን በስኬት አጠናቅቀናል፤ ወደ ቀይ ባሕር ተመልሰናል !

13

የኢትዮጵያ ታሪክ ከዓባይ እና ከቀይ ባሕር ጋር የተሳሰረ ነው። የዓባይ እናት ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ታሪክም ከእርሷ ነጥሎ ማየት አይቻልም። ነገር ግን ታሪካዊ ጠላቶቿ እነዚህን የታሪኳ ማጠንጠኛ የኾኑ ውኃዎችን እንዳትጠቀም ብዙ ደባዎችን ሠርተዋል።

አሁን ግን ሀብቶቿን ለመጠቀም ትክክለኛው መንገድ ላይ ናት። “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” ሲባል የነበረውን የቁጭት ታሪክ በመቀልበስ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ በቤቱ እንዲያድር አድርገውታል። በጋራ አልምተው ተጠቃሚ ኾነዋል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሃብት የኾነው ቀይ ባሕርም እናቱን ናፍቋል።

የውኃ እና ኢነርጅ ሚኒስትር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር) የሕዳሴ ግድቡ የኃይል ተደራሽነትን አሳድጓል ብለዋል። እንደ ሀገር 63 በመቶ የኃይል ተደራሽነት ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ትልቁ የኃይል ምንጭ የኾነውን የውኃ ሃብትን ማበልጸግ እንደሚገባም አንስተዋል። የውኃ ሃብትን መረጃ በአግባቡ ለመያዝ፤ የውኃ ፍሰት መጠንን ለመለየት በቴክኖሎጅ የታገዘ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም አንስተዋል።

በአፍሪካ እና በዓለም ሀገራት ኢትዮጵያ የቀጣ የኃይል ቋት መኾኗ እየታመነ መምጣቱን ገልጸዋል። በተግባር የኃይል ቋት መኾኗን ማሳየት ተችሏል ብለዋል። ከራሷ ባለፈ ለጅቡቲ፤ ለኬኒያ፤ ለታንዛኒያ እና ለሌሎች ጎረቤት ሀገራት የኃይል አቅርቦትን ተደራሽ ማድረጓንም ገልጸዋል።

በሀገሪቱ እየታየ ያለው ከፍተኛ ዕድገት የኃይል አቅርቦትን የሚፈልግ በመኾኑ ይበልጥ ለማሳደግ ይሠራል ነው ያሉት።

ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ሲወስኑ መቆየታቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወት እና የፖለቲካ ሂደት ከዓባይ እና ቀይ ባሕር ጋር የተሳሰረ መኾኑንም ተናግረዋል። ቀይ ባሕር የውኃ ጉዳይ ብቻ ሳይኾን የሕልውና ጉዳይ ነውም ብለዋል።

በርካታ መሪዎች ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታጣ መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰዋል። በሁለቱ ውኃዎች ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ዋጋ ከፍለዋል ነው ያሉት። ከባሕር በር ርቆ መኖር አይታሰብም ብለዋል።

በዓባይ ጉዳይ በግብርና ልማት እና በኃይል ማመንጫ እንዳትጠቀም የኢትዮጵያ እጆች እና አዕምሮ እንዲታሠሩ ሲሠራ መቆየቱን ያነሱት ሚኒስትሩ የዓባይ ተፋሰስ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ሕልውና ናቸው ብለዋል። ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በመገንባት የዘመናት የሕዝብ ሕልምን እውን ማድረግ መቻሏን አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛ ኃይል በማመንጨት ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት በማካፈል የሕዝብን ሕልም እውን ማድረግ ችሏል ብለዋል። የዛሬው ትውልድ ከሁለቱ ውኃዎች ውስጥ የአንደኛውን ሴራ በማፍረስ ማሳካት ችሏል ነው ያሉት።

በሴራ የተወሰደውን የባሕር በር በሰላማዊ መንገድ ለማስመለስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ባሕር በር የፖለቲካ ጉዳይ ሳይኾን ለትውልድ የሚሻገር የሕዝብ ጥቅም እንደኾነ ነው የተናገሩት።

ሕዳሴ ላይ ያሳየነውን አንድነት በማጠናከር የባሕር በር ለማስመለስ በጋራ መታገል ይገባናል ብለዋል።

#አሚኮ #ባሕር_በር #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_08_2018ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleወጣትነትን ለሀገር ሕልውና እና ለልማት ማዋል ይገባል።
Next article🇪🇹በምክክሩ ሂደት ላይ ለምን ልዩነቶች ተስተዋሉ?