ክልል አቀፍ ፈተናውን 100 ያመጣችው የቀለም ቀንድ ከኮምቦልቻ!

5
በሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ፈተናዎች ላይ 100 በመቶ ውጤት ማስመዝገብ ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ የስድስተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናን 100 በመቶ ያመጣችው የኮምቦልቻዋ የቀለም ቀንድ ግን አድርጋዋለች።
‎በ2018 ዓ.ም በተሰጠው የስድስተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች 100 በመቶ በማምጣት ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግባለች፡፡
‎የኮምቦልቻ ቁጥር ሁለት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዋ ነጅዋ ሰይድ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ በትምህርቷም ኾነ በሥነ-ምግባሯ የላቀች ተወዳዳሪ መኾኗን ወላጆቿ እና መምህራን ይናገራሉ፡፡
‎የተማሪ ነጅዋ የስኬት ምስጢሩም ለረጅም ሰዓታት ለጥናት ከመቀመጥ ይልቅ ውጤታማ የሚያደርገውን በክፍል ውስጥ ጥሩ ተሳትፎ በማድረግ የትምህርት ርዕሰ ጉዳዩን በትክክል መረዳት የሚያስችላትን የተሳትፎ ስልት መከተሏ እንደኾነ ተናግራለች፡፡
የምታነበውን በትንሽ በትንሹ ማስታወስ እና መልሶ መጻፍ የምትከተለው ዘዴ ነው፡፡ ለጥናት የምትመርጠው ጊዜም አዕምሮዋ ትኩስ በኾነበት ከጠዋቱ 11:00 ጀምሮ መኾኑን ገልጻለች።
‎የወደፊት ትልቅ ሕልሟ የሥነ-ክዋክብት ተመራማሪ እና የሶፍትዌር መሐንዲስ መኾን እንደኾነ ተናግራለች። እንደ ናሳ ባሉ ትልልቅ የዓለማችን የአስትሮኖሚ ኩባንያዎች ውስጥ መሥራት እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያሉ ጉድለቶችን የሚቀርፍ አዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማበርከት ትልቁ ሕልሟ እንደኾነም ነው የገለጸችው፡፡
‎የነጅዋ አባት አቶ ሰይድ እሸቴ ቤተሰቡ የጥናት መርሐግብር በማውጣት እና ክትትል በማድረግ እገዛ እንደሚያደርግላትም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች እንዳይበልጧት ሲያበረታቷትም የምትወዳደረው ከራሷ ጋር መኾኑን ትነግረኛለች ይላሉ አባቷ፡፡
‎ወላጅ እናቷ ወይዘሮ ፋጡማ ኢብራሂም በበኩላቸው ቤት ውስጥ ቀለል ያሉ ሥራዎችን እንደምትሠራ አንስተዋል፡፡ ለትምህርቷ ትኩረት እንደምትሰጥም ገልጸዋል፡፡
‎የኮምቦልቻ ቁጥር ሁለት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር እንድሪስ አበበ ተማሪ ነጅዋ ከአንደኛ ክፍል ጀምራ እጅግ በጣም ተወዳዳሪ፣ በሥነ-ምግባር የታነጸች እና ጠንካራ ተማሪ መኾኗን አንስተዋል፡፡ በከተማ ደረጃ በተደረገው የቀለም ትምህርት ውድድር አንደኛ መውጣቷንም ተናግረዋል፡፡
የተማሪ ነጅዋ ከፍተኛ ውጤት ከእራሷ ጥረት በተጨማሪ በቤተሰቦቿ እና በመምህራኖቿ የጋራ ጥረት የተገኘ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleግብርናውን ወደ ኢንዱስትሪ የማሸጋገር ተልዕኮ !
Next article​ “ሕይወት እንዳዳንኩ ሳስበው የማገኘው ውስጣዊ እርካታ ወሰን የለውም” ደም ለጋሽ