
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ መሪዎች እና አባላት በማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የባሕር ዳር ጄኔራል ፍሌክሴብል እና ፋውንደሪ ፋብሪካን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ዝግጁነት ማዕከል ምክትል መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ንብረቱ ሞላ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ከትልልቅ እስከ አነስተኛ ማሽኖችን ድረስ በራሱ አቅም በማምረት ለማኅበረሰቡ እያቀረበ ያለ ፋብሪካ እንደኾነ መታዘባቸውን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ምክትል አዛዥ ኮማንደር መኳንንት አድማስ የብረት ፋብሪካው ብረት ከማቅለጥ ያለፈ የተለያዩ ማሽኖችን በማምረት ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መኾኑን እንደተመለከቱ ተናግረዋል። ለግብርና እና መሰል ፋብሪካዎች የሚኾኑ ማሽኖች ማምረት መቻሉንም አድንቀዋል።
ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ከውጭ ምንዛሬ የሚያድኑ፤ ችግር ፈቺ የኾኑ እና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ማሽኖችን እያመረተ እንደተመለከቱም ተናግረዋል። ኢንዱስትሪዎች ሳይስተጓጎሉ እንዲያመርቱ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ማኅበረሰቡ የምርቱ ተጠቃሚ እንዲኾን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠሩም አመላክተዋል።
በማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የባሕር ዳር ጄኔራል ፍሌክሴብል እና ፋውንደሪ ፋብሪካ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ጥበቡ ደምስ ፋብሪካው የብረት ማቅለጫ፣ ማስተካከያ፣ መገጣጠሚያ እና ማምረቻ ክፍሎች እንዳሉት ተናግረዋል።
የመኖ ማቀነባበሪያ፣ የላይም ስቶን ፋብሪካ፣ የስኳር ፋብሪካ እና የሲሚንቶ ፋብሪካ መለዋወጫ ማሽኖችን እያመረተ መኾኑንም አንስተዋል።
ፋብሪካው የክልሉ መንግሥት የልማት ድርጅት እንደመኾኑ የክልሉን ግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የማሸጋገር ትልቅ ተልዕኮ ይዞ እየሠራ ነው ብለዋል።
ከተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር በመስራት እና የተሻለ ልምድ ያላቸውን የውጭ ዜጎች በመቅጠር የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ፤ የስኳር ፋብሪካዎችን በማሽን ለመመገብ እና ፋብሪካውን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ፋብሪካው ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መኾኑን የተናገሩት ሥራ አሥኪያጁ በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ከ640 በላይ ሠራተኞች አሉት ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
