
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁ ማኅበራት የብሎክ ዕጣ የማውጣት መርሐ ግብር አካሂዷል።
የመኖሪያ ቤት ዕጣ ማውጣት ላይ የተገኙት የምሥራች አበጀ በከተማዋ የነዋሪ ፍሰት በመጨመሩ በቤት ኪራይ እና በኑሮ ውድነት አስቸጋሪ ወቅት ማሳለፋቸውን አንስተዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ በአጭር ጊዜ የመኖሪያ መሥሪያ ቦታ በመስጠቱ አመስግነዋል። ቤት ለማግኘት በርካታ ዓመታት የሚወስደውን ጊዜ በማሳጠር በአጭር ጊዜ ተደጋጋሚ ማጣራት በማከናወን ማኅበረሰቡን የቤት ተጠቃሚ በማድረጉ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ማኅብረሰቡን የቤት ባለቤት ለማድረግ መንግሥት ሢሠራ ኅብረተሰቡ ደግሞ ቁጠባን በማሳደግ በተሠጠው ቦታ መሥራት አለበት ነው ያሉት።
የቤት መሥሪያ ቦታ ዕጣ ተጠቃሚው ሳሙኤል መኮንን መንግሥት ሠራተኞች እና የጸጥታ አካላትን የቦታ ተጠቃሚ ለማድረግ በመሥራቱ አመስግነዋል። የመንግሥት ሠራተኞች በቤት ችግር ምክንያት ለፈተና ይጋለጡ እንደነበርም አንስተዋል። መንግሥት ሠራተኞች የቤት ባለቤት መኾናቸው የኑሮ ውድነት የሚያሳድርባቸውን ጫና የሚቀንስ መኾኑንም ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳር ከተማን ለነዋሪዎቿ የተመቸች ማድረግ የሚቻለው በኮሪደር ልማት፤ በከተማ ውበት፤ በጣና ዳር ልማት ብቻ ሳይኾን ነዋሪዎቿን የቤት ባለቤት ማድረግ ሲቻልም ነው ብለዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች እና የተለያዩ የልማት ድርጅት ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ማግኘታቸውን ገልጸዋል። የቤት መሥሪያ ቦታ ያገኛችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። በቀጣይ በተለያዩ የቤት ልማት ሥራዎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
