
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን እና በተመረጡ ተቋማት መካከል ውጤታማ የሚዲያ ቁጥጥር ሥርዓትን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ስምምነቱ ያስፈለገው የሚዲያ ተቋማት ቁጥር እያደገ መምጣት፣ የቴክኖሎጂ ልማት እና ሕግ የማስፈጸም ሥራዎችን በተናጠል መሥራት ውጤታማ ባለመኾኑ በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ በመኾኑ ነው ብለዋል።
እስካሁን ከ16 ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት መታቀዱን ተናግረዋል። ከተቋማቱ መካከል የብሔራዊ መረጃ እና ደኅነነት አገልግሎት፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች ተቋማት ይገኙበታልም ነው ያሉት።
ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት፣ የሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ ሕጎችን ማስፈፀም እና መረጃ ልውውጥን ማጠናከር ዋና ዋና የትብብር መስኮች ናቸው ብለዋል።
የተቋማቱ ትብብር የጥላቻ ንግግር እና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።
ትብብሩ የመረጃ ልውውጥን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ እና የሚዲያ ይዘት ክትትል እና የሞኒተሪንግ አሠራርን በመዘርጋት ውጤታማ የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል ።
ዘጋቢ : ሠላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
